
ደሴ: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ሴት የሥራ ኀላፊዎች በኮምቦልቻ ከተማ በልማት ኅብረት የተሠሩ የልማት ተግባራትን ጎብኝተዋል። በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በከተማ ግብርና፣ በከብት ርባታ እና በእንጀራ መጋገር የተሰማሩ የሴት ልማት ኅብረት አደረጃጀት፣ የዝቅተኛ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሕፃናት ማቆያ ናቸው የተጎበኙት።
ከተለያዩ ክልሎች ለልምድ ልውውጥ የመጡ ሴት መሪዎች በኮምቦልቻ ከተማ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት የተሠራው ተግባር ውጤታማ ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ “ሴቶች በግል ከሚያመጡት ውጤት ይልቅ ተደራጅቸው ዕውቀታቸውን እና ሀብታቸውን በጋራ ተጠቅመው የጋራ ውጤት እንዲያመጡ ወጥ የኾነ አሠራር ተቀርጾለት ወደ ተግባር ተገብቷል” ነው ያሉት።
ሴቶች ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በትምህርት፣ በጤና፣ በሰላም ግንባታ እና በሌሎቹም የላቀ አስተዋጽዖ እንዲኖራቸው በእቅድ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ሞዴል ልማት ኅብረት እና ሞዴል ቀበሌን መፍጠር ዓላማን በማድረግ በሀገር ደረጃ የተነደፈውን ግብ ለማሳካትም ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የልምድ ልውውጡ መዘጋጀት በአማራ ክልል ሞዴል የሴቶች ልማት ኅብረት ከኾኑት የተሻለ ልምድ ለመውሰድ እና ተሞክሮውን ለማስፋት እንደኾነም ተገልጿል። ከልምድ ልውውጡ ባሻገር ሴቶች ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ እና ሁለተናዊ ተሳትፏቸው እንዲረጋገጥ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
በልምድ ልውውጡ ከተሳተፉት መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ዓለምነሽ ይባስ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ካሰች ኤልያስ በትንሽ ቦታ ላይ በቋሚ እና ፈጥነው የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችን አልምተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የኾኑ ሴቶችን በመጎብኘታቸው ልምድ እንደወሰዱ አስረድተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አመዘን ሙሀመድ በከተማ አሥተዳደሩ ከ49 ሺህ በላይ የሴቶች ልማት ኅብረት ለማደራጀት ጥረት ተደርጓል ብለዋል። ሴቶች ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲኾኑ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያብራሩት ኀላፊዋ ውጤታማ የኾኑ የልማት ኅብረቶችን ልምድ በማለዋወጥ ተግባሩን ለማስፋት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ከሲዳማ ክልል የተውጣጡ ሴት የሥራ ኀላፊዎች እና የሴቶች ልማት ኅብረት አደረጃጀት መሪዎች ተሳትፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን