
እንጅባራ: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር ሠራተኞች “የጥፋት እጆችና መዘዞቹ “በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል። በመድረኩ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በደረሰው ጉዳትና ከችግሩ መውጫ መንገዶች ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ የእያንዳንዱን ግለሰብ ቤት ያንኳኳ፣ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል። መድረኩ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ እየደረሰ ባለው ጉዳት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና ከችግሩ መውጫ መንገዶች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል እንደሆነም አንስተዋል።
ሰላም በምኞት ሳይሆን በጋራ ትብብር የሚፀና ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሁሉንም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) እየተካሄደ ያለው ግጭት ከዚህ በላይ ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።
ለግጭትና ብጥብጥ የሚጋብዙ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚረጩ የተዛቡ መረጃዎችን መመዘንና ለሌሎችም ማስገንዘብ ከዩኒቨርሲው ማኅበረሰብ ይጠበቃል ነው ያሉት። የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስና ዜጎችን ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ ክልከላ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያላቸውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!