“ሰርክ ሰላም በሚሰበክበት አካባቢ ለምን ሰላም ደፈረሰ? ይህን መጠየቅ አለባችሁ ” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

12

ወልድያ: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከላሊበላ ከተማ፣ ከላስታ እና ከቡግና ወረዳዎች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በላሊበላ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የርእሰ መሥተዳድሩ የአደረጃጀት አማካሪ ፍስሀ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ለሊቃውንት ከተማ ስለ ሰላም ለመምከር መምጣት ሕጻን አባቱን ለመምከር የመሻት ያህል ነው ብለዋል። ላሊበላ ከተማ ታሪካዊ እና ሥነ መንግሥታዊ ሃብት ባለቤት እንደኾነም አንስተዋል። በመድረኩ የሚሳተፉ ልሂቃን አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የዚህ ጥበብ ባለቤቶች ናቸው፤ ለእናንተ ስለ ሰላም መምከር ይከብዳል ነው ያሉት።

የላሊበላ አይነት ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ምክንያት ላይ ተመሥርተው ምንጊዜም መንግሥታዊ አሥተዳደር የሚመርጡ ናቸው ብለዋል። የቀደመ ሥልጣኔ ትንተና ሲያስፈልግ ማጣቀሻዎቹ የላሊበላ አይነት ማስረጃዎች ናቸው ነው ያሉት። ስር የሰደደ የሥነ መንግሥት ታሪክ ያለው፣ በክርስትና ሃይማኖት ቅዱስ የኾነ፣ ለዓለም ድንቅ አሻራ ያሳረፈ፣ ሰርክ ሰላም በሚሰበክበት አካባቢ ለምን ሰላም ደፈረሰ? ይህን መጠየቅ አለባችሁ ብለዋል።

ሰላም እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ሕዝብ እና መንግሥት የሰላም መደፍረስ ምክንያት እና መፍትሔ ላይ ከልብ መነጋገር ይጠበቅብናል ነው ያሉት። “የገጠመንን ፈተና ምንጭ መፈተሽ እና መመርመር ይኖርብናል” ብለዋል። ተግባብቶ አቋም ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ማንም በሚረጨው አሉቧልታ ወሬ የሚረበሽ ሕዝብ መኾን እንደማይገባም አሳስበዋል።

የጸጥታ ችግሩ አጠቃላይ ክልሉን ቢጎዳም የላሊበላ ሕዝብ ላይ ግን ጉልህ ችግር አሳድሯል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ላሊበላ የገቢ ምንጩ ቱሪዝም ላይ የተቆራኘ ነው፣፣ ሌሎች የክልሉ አከባቢዎች ተጓዳኝ የግብርና እና መሰል የኢኮኖሚ መሠረቶች እንዳሏቸው ገልጸዋል። ቱሪዘም ሰላም ይሻልና የላሊበላን ሰላም ማደፍረስ እና የሰላም ችግሮችን መደገፍ በራስ ላይ እሳት ማንደድ እና ራስን ማጥፋት በመኾኑ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች፦
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዛሬ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን ጎበኙ።