
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ስለ ሰላም የሚመክር ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ከሰኔ 4/2017 እስከ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል። ዝግጅቱን የሚያደርጉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሐጂ መስዑድ አደም ለአሚኮ እንደገለጹት የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ሰላምን መስበክ እና መከባበርን ማስተማር ነው። እንደ ሀገር እየተደረጉ ያሉትን ሰላም አምጭ ጥረቶችን ማገዝ ደግሞ ከሃይማኖት ተቋማት ይጠበቃል ብለዋል ሐጂ መስዑድ።
የሕዝቦችን አንድነት በመፍጠር ስለሰላም፣ መከባባር፣ አንድነት እና ፍቅር ጉባኤው በስፋት እና በጥልቀት ይመከራል ነው ያሉት። አኹን ላይ እንደ ሀገር ካጋጠመው የሰላም እጦት እንዴት መውጣት እንደሚቻል በጉባኤው የመፍትሔ ሐሳብ ይቀርብበታል ብለዋል። ሐጂ መስዑድ በጉባኤው የሚንጸባረቁ ብዝኀ ሐሳቦች ማደማደሚያቸው
ሁሉንም አካል ለሰላም እንዲነሳሳ የሚያደርጉ የሚያነቃቁ ይኾናሉ ተብሎ ተስፋ መደረጉንም ተናግረዋል። መንግሥትም ኾነ በጫካ የሚገኙ ወገኖች ስለሰላም ተነጋግረው እና ተደማምጠው ወደ ሰላም እንዲመጡ የሚያግዝ ጉባኤ ነውም ብለዋል። የመገናኛ ብዙኀንም ሰላም አምጭ እና ሰላምን ሊገነቡ የሚችሉ አዎንታዊ ዜናዎችን እና ዝግጅቶችን በማሰራጨት ሀገራዊ እና ሞራላዊ ግዴታዎቻቸውን እንዲወጡ ሐጂ መስዑድ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን