
ደሴ: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ፣ የደቡብ፣ የሲዳማ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና የልማት ኅብረት ተጠቃሚ ተወካይ ሴቶች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በሴቶች የልማት ኅብረት የተሠሩ ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ሥራቸውን ካስጎበኙት መካከል አንዷ የኾኑት ወይዘሮ አሚና አሊ የሴቶች የልማት ኅብረት አደረጃጀት ከመጣ በኋላ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ በማምጣት የአኗኗር ዘይቤያቸው መሻሻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የሥራ ጫና እንደነበረባቸው እና አሁን ላይ ሥራን ከቤተሰባቸው ጋር ተከፋፍለው እና ተጋግዘው በመሥራት በአንስተኛ ማሳ ለቤተሰባቸው የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎች እያመረቱ መኾኑን ወይዘሮ አሚና ተናግረዋል።
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡት ወይዘሮ ሀስኒያ ሱለይማን ባዩት ሥራ መደሰታቸውን እና ተሞክሮ መውሰዳቸውን ገልጸው በቀጣይ ለሚመሯቸው የልማት ኅብረት ልምዱን በማካፈል የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የልማት ኅብረቱ በቁጠባ ረገድ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው እና ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ እንደ የእህል ወፍጮ እና ሌሎች ተቋሞችን መሥራት እንደሚቻልም ተሞክሯ መውሰዳቸውን ነው ያብራሩት፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የሴቶች የልማት ኅብረት ሪፎርም ከተሠራ በኋላ በገጠርም በከተማም ባሉ ሴቶች ሁሉን አቀፍ በኾነ መልኩ አደረጃጀቱ መፈጠሩን አስታውቀዋል።
አደረጃጀቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅም መፍጠሩንም ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ከየሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕጻናት መብት ጥበቃ ሥራ አሥፈፃሚ ዘቢደር ቦጋለ በሀገር አቀፍ ደረጃ አደረጃጀቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅም መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ተሞክሮውን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት እና ማጠናከር እንደሚገባም አፈጉባኤዋ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦መሐመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን