የፋይናንስ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነትን በማስፈን ልማትን በአሳታፊነት እና ዘላቂነት ማረጋገጥ ይቻላል።

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን መሪዎች እና ባለሙያዎች በመንግሥት ፋይናንስ አሥተዳደር ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ የገንዘብ ቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ደሳለኝ ዓለምነህ የፋይናንስ ግልጸኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የመንግሥት ባለበጀት መስሥሪያ ቤቶችን እና የገንዘብ ቢሮን ተግባር እና ኀላፊነት ማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡

ተቋማትም የተመደበላቸውን ሃብት በአግባቡ የሚያሥተዳድሩበትን ሁኔታ በመፍጠር ለሚስተዋሉ ችግሮችም የጋራ መፍትሄ ለማስቀመጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በጀት ስለሚጠይቁበት እና ገንዘብ ቢሮም አደራጅቶ ልማትን ማዕከል አድርጎ በማዘጋጀት በምክር ቤት ስለሚያጸድቅበት እና የበጀት ድልድል እና አሥተዳደር ስለሚኖርበት ሁኔታም ግልጽነት ለመፍጠር መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን ሥልጠናው በጀት እንዴት ወደ ክልል፣ ዞኖች እና ወረዳዎች እንደሚከፋፈል፣ ድርሻችንም ምን እንደኾነ አውቀን አስተዋጽኦ እንዲኖረን ያደርጋል ብለዋል፡፡

የልማት ፍላጎታችን ትልቅ እንደ መኾኑ የበጀት ፍላጎታችን ትልቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የገቢ አሰበሰባችንም ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክልሉ ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም ገቢን ማሳደግ እንደሚገባም መረዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የፋይናንስ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን በየተቋማችን በጀትን በጋራ በማጽደቅ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ አሳታፊ እና ግልጽ በኾነ መንገድ ሕዝብን ጨምሮ ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ እና በፕሮጀክቶች ላይም ለኅብረተሰቡ ግልጽ ማድረግ ሥራ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት አበበ እንቢአለ በበኩላቸው ሥልጠናው ውስን ሃብትን በአግባቡ ለማሥተዳደር የሚመለከተው አካል በዘርፉ ላይ ግልጽነት እንዲፈጠርለት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ትኩረት ለሚሰጣቸው ዘርፎች የሃብት ምደባን እና አጠቃቀምን በተመለከተም በእቅድ በመመራት ውጤታማ ስለማድረግ ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ግልጸኝነት ሲፈጠርም ችግሮች ይቀንሳሉ ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኀላፊ ትብለጥ መንገሻ የተሰጠው ሥልጠና ሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሕዝብ ዐይን እና ጆሮ ኾኖ ስለሚያገለግል በፋይናንስ አሥተዳደር፣ አሠራር እና ተጠያቂነት ግልጽ ኾኖ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ሥልጠናው አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞቹ ለሚመሩት ተቋም የበጀት አጠቃቀም እና አሥተዳደር በደንብ አውቀው ለተዋረድ ተቋማትም ድጋፍ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ለተቋማት እና ለሕዝብም የፋይናንስ አሥተዳደር እና አሠራር ምን እንደኾነ ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅም እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኞች ወደ ተቋማቸው ተመልሰውም ለአመራሮች እና ለፋይናንስ አሥተዳደር ባለሙያዎች ግንዛቤ እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ብለዋል ወይዘሮ ትብለጥ፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) የተሰጠው ሥልጠና የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን መሪዎች እና ባለሙያዎች በፋይናንስ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የመንግሥትን በጀት በአግባቡ ተጠቅሞ ልማት ላይ ለማዋል አሠራሩን ለማሳወቅ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

ለሕዝብ ልማት የተመደበ በጀትን በአግባቡ ተጠቅሞ በመሥራት ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲኾን የበጀት ምንጭ፣ አሠራር እና ዓላማ በየደረጃው አሥተዳደር አማካይነት በሕዝብ ውይይት ተደርጎበት እና መተማመን ተደርሶበት በልማቱም ላይ ሕዝብ አጋዥ እንዲኾን የፋይናንስ የግልጸኝነት እና ተጠያቂነት አሠራርን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን አካላት መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ ባላቸው ሚና ተጠቅመው እንዲሠሩ ግንዛቤ መፈጠሩን ነው ዶክተር ጥላሁን የተናገሩት፡፡

በወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች የፋይናንስ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ውይይት መከናወን ከጀመረ መቆየቱን የተናገሩት ዶክተር ጥላሁን የበጀት መጠንን፣ የገቢ ምንጩን እና በጀቱ ለምን እንደሚውል በማሳወቅ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡

የበጀት ድልድልን ሕዝቡ በግልጽ እንዲያውቅ በፖስተር መለጠፍ የጀመሩ ወረዳዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ሠልጣኞችም መረጃ ለሕዝብ በሚሰጡበት ጊዜ ሕዝብ ስለበጀቱ መረጃ የማወቅ መብት ያለው መኾኑን ተረድተው እንዲያሳውቁ ግንዛቤ ለመፍጠር መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የምርጫ ምዝገባ ማስጀመሪያ (ሹራ)እያካሄደ ነው።
Next articleየሴቶች ልማት ኅብረት አደረጃጀት የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ተሞክሮ የሚኾን ሥራ ሠርቷል።