
ሁመራ: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት ቅንጅታዊ ተሳትፎ የሕዝቡን ችግር የሚቀርፉ መሠረተ ልማቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት እየገቡ ነው።በቃብትያ ሁመራ ወረዳ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የኾነው የቃብትያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከጥቂት ወራት በፊት ግንባታው ተጠናቅቆ መመረቁ ይታወሳል።
ሆስፒታሉን አገልግሎት ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። የክልሉ ጤና ቢሮ እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ኅብረተሰቡ የሚያገኘውን የጤና አገልግሎት እያሳደገው ነው ሲሉ የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ስማቸው ግደይ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ጤና ቢሮው ከሰሞኑ ያደረገውን የአምቡላንስ ድጋፍም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከለውጥ ማግሥት ጀምሮ በርካታ ድጋፎች መደረጋቸውን በማስታውስ የጤና ተቋማቱ ቁሳቁሶችን በአግባቡ በመጠቀም ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እየተሠራ ነውም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት እና ጤና ቢሮ ለዞኑ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ገልጸዋል። ግንባታው የተጠናቀቀውን ሆስፒታል ወደ ሥራ የማስገባት ሂደቱ ውጤታማ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሆስፒታሉን በቁሳቁስ እና በሰው ኀይል የማደራጀት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ኅብረተሰቡ የተቋሙ ባለቤት በመኾኑ ድጋፍ እና ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ባለሙያዎቹ በተሰጣቸው ኀላፊነት ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ናቸው።
ሕዝቡ እና የሃይማኖት አባቶች ከመሪዎች ጋር በመተሳሰብ እና በመመካከር ሰላሙን መጠበቅ እና ልማቱን ማስቀጠል እንደሚገባም አንስተዋል። ሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ የተመደበለት ሲኾን የባለሙያ ቅጥር በመፈጸም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን