የሀሠተኛ የትምህርት ማስረጃ መስፋፋት የዛሬን ብቻ ሳይኾን የነገን የሀገር እና ትውልድ ተስፋ የሚያጨልም ነው።

26

ደሴ: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን የ10 ወራት የሥራ አፈፃጸም ግምገማ እና በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ አተገባበር ላይ ያተኮረ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ሪፎርሙ ጥራት እና ብቃት ያለው ተቋም እና የሰው ኀይል በመገንባት ለኅብረተሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና የሲቪል ሰርቪስ ዳኞች በሪፎርሙ አተገባበር ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ይዘው በተሟላ ዝግጅት ወደ ሥራ እንዲገቡ መድረኩ መመቻቸቱ ተገልጿል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ብዙነሽ ሰይድ በከተማ አሥተዳሩ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ ሥልጠናዎችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ነው ያነሱት፡፡

ሲቪል ሰርቪሱ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በትኩረት መሥራት ያስፈላጋል ያሉት ኀላፊዋ በቀጣይም የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት በትኩረት እንሠራን ብለዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ በሪሁን ተገኘ እንደገለጹት በዞኑ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ላይ የተመዘገቡ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም አሁኹንም ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በኩል ክፍተቶች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡

የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በነበረው ጀምር በርካታ የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ሂደቶች እንደነበሩ ጠቅሰው አኺን በተሰጠው ትኩረት እና አቅጣጫ መሠረት ለመተግበር ቁርጠኛ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ተወካይ ፈለቀ ኀይሌ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በጦርነት ወቅት በደረሰው ውድመት ሳቢያ አገልግሎት ለመስጠት የተፈጠሩ ክፍተቶች መኖራቸውን በማንሳት በተቻለ መጠን ችግሮቹን ተቋቁሞ ለማገልገል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የሀሰተኛ የትምህርት ዝግጅት ማጣራት ላይ ቴክኒካል ሥልጠና ወስደው መሪዎች እና ሥራውን የሚያስተባብሩ ተቋማት ግንባር ቀደም ኾነው የራሳቸውን ማስረጃ በማቅረብ ለሌሎች አርዓያ መኾን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በምክትል ቢሮ ኀላፊ ማዕረግ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ቢሮ አማካሪ ተፈሪ ካሣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በፍጥነት እና በጥራት ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉን አቀፍ ሥልጠናን በመስጠት ተግባራዊ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሀሠተኛ ትምህርት ማስረጃ መስፋፋት የዛሬን ብቻ ሳይኾን የነገን የሀገር እና ትውልድ ተስፋ የሚያጨልም በመኾኑ በብቃቱ ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰዋል። ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተፈተነ እና በክህሎት የበለፀገ ባለሙያ እንዳይኖር በማድረግ የመልካም አሥተዳደር ችግርን እየፈጠረ እና ጫናን እያሳደረ በመኾኑ በትኩረት የሚሠራበት ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።

እንደ ክልል እስካኺን መረጃ የማሠባሠብ እንጅ የተጣራ ግኝት አለመኖሩን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ መረጃን የመደበቅ እና የማጓተት ሥራን የሚሠሩ ቢኖሩም በቁርጠኝነት በመሥራት የመሪዎችን አጠናቅቆ በሂደት የሁሉንም ባለሙያዎች የማጣራት ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ የልማት ሥራዎችን ተመለከቱ።
Next articleየቃብትያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ወደ ሥራ የማስገባት ሂደቱ ውጤታማ ነው ተባለ።