ዓሣን እንደ ጎመን!

24

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ዓሣ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፤ ዶሮ መረቅማ ከወዴት አባቴ” የሚለው የድምጻዊ አሰፋ አባተ ዜማ አሁን ላይ ቅቡል አይመስልም፡፡ በዚያ ዘመን ዓሣ እንደ ዶሮ ወጥ ካሉ ልዩ እና ውድ ምግቦች ቢመደብም እንደ ዓባይ እና ጣና ባሉ ታላላቅ የውኃ አካላት እንጂ በሌላ ቦታ አይገኝም ነበር፡፡

“ዓሣን መብላት በብልሃት” ከሚባለው ሥነ ቃል ጀምሮ የዓሣ ዘይት የጠጣ ሕጻን አዕምሮው ፈጣን ይኾናል እስከሚባለው ምክረ ሃሳብ ድረስ ዓሣ ለአዕምሮ ብስለትም ኾነ ለቅንጦት ተፈላጊ ኾኖ ኖሯል እንደልብ ባይገኝም። ባለው የፕሮቲን ይዘት ዓሣን መመገብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሥነ ምግብ እና የጤና ባለሙያዎች ቢመክሩም ለበርካታው ኢትዮጵያዊ ዓሣን ለማግኘት ከገንዘብም በላይ አካባቢ የሚወስነው ኾኖም ኖሯል።

ዛሬ ላይ ግን በመላ ኢትዮጵያ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ከሚገኝ የግብርና ዘርፍ ውስጥ አንዱ ኾኗል። ፍኖተ ካርታ፣ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና ፓኬጅ ተዘጋጅቶለት ከተሜው ጭምር እንዲጠቀምበት እየተደረገ ነው። ዓሣን እንደ ጎመን በጓሮ የሚያገኙት ምርጥ ምግብም ኾኗል። በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዓሣ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አበበ ፈንታሁን በዓሣ ግብርና (ዓሣን በኩሬ) ማልማት ያለውን ጠቀሜታ፣ ሥራው ያለበትን ደረጃ እና ትኩረቶችን አብራርተውልናል።

ዓሣን በኩሬ የማልማት ሥራ በኢትዮጵያ በ1970ዎቹ አካባቢ በግብርና ምርምር ተቋማት እንደተጀመረ እና በአማራ ክልል ደግሞ በ1996 ዓ.ም ጀምሮ የዓሣ ግብርና ተጀምሯል። አነስተኛ የስፋት መጠኑ 150 ካሬ ሜትር የኾነ የውኃ ኩሬ በማዘጋጀት እና የዓሣ ጫጩቶችን በመጨመር አሳድጎ መጠቀም የተለመደ የዘርፉ ሥራ መኾኑንም አንስተዋል።

ሥራው ዓሣን ከተፈጥሮ የውኃ አካላት የራቁ ሁሉ ለማግኘት፣ ለመመገብ እና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትም እንደሚያስችል ገልጸዋል። በሁሉም አካባቢ ሊከናወን የሚችለው የዓሣ ግብርና በየጊዜው እየሰፋ እና በከተሞች ሳይቀር እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል። ወይዘሮ ገነት አበባው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ሲኾኑ በገነት፣ ዮሴፍ እና ጓደኞቻቸው ማኅበር ተደራጅተው በጥምር ግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ከዚህ ውስጥም ዓሣን በኩሬ ማልማት አንዱ ነው።

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ዓሣን በኩሬ ማርባት ጀመርን ያለችው ገነት ከስድስት ወር በኋላ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጻለች። ከአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ከዶሮ እርባታ ሥራቸው ላይ ዓሣን በመጨመር ሥራውን ተመጋጋቢ አድርገውታል። እነ ገነት ሥራው አዋጭ በመኾኑ ተጨማሪ ኩሬ አዘጋጅተው ዓሣ እያረቡ ነው፡፡ ከዓሣ ምርምር ማዕከል ያገኙትን የዓሣ ጫጩት ጨምረው አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በስድስት ወሩ ለምርት ደርሶላቸዋል፡፡

ዓሣ ተመጋቢ ስለኾንን የምርቱን ጠቀሜታ እናውቃለን። እናም ከመግዛት መውጣት ብቻ ሳይኾን ትኩስ ዓሣ ከጓሮ ማግኘት ያስችላል ይላሉ ወይዘሮ ገነት፡፡በአማራ ክልል በ30 አርሶ አደሮች የተጀመረው የዓሣ ግብርና ልማት ዛሬ ላይ በብዛት እና በውጤታማነት በመከናወን ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ 600 አርሶ አደሮች በዘርፉ እንደተሰማሩ የጠቀሱት አቶ አበበ 186 ቶን የዓሣ ምርት በዓመት መመረቱንም ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚገኘው የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤትም ለዓሣ ልማት ምቹ የኾኑ አካባቢዎችን የመለየት፣ ግንዛቤ የመፍጠር፣ አቅም የመገንባት፣ የሙያ ድጋፍ እና ሌሎች ሥራዎችን እየከወነ ነው። አሠራሩ እስኪለመድ የዓሣ ጫጩቶች በነጻ እየቀረቡ መኾኑን የገለጹት ባለሙያው በዘንድሮው በጀት ዓመት እንኳ 900 ሺህ የዓሣ ጫጩት ለማቅረብ ታቅዶ ይህ ቃለመጠይቅ እስከተሠራበት ጊዜ ድረስ 665 ሺህ መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አበበ ገለጻ ዓሣን በኩሬ ማልማት ገና ያልተሠራበት እምቅ ሃብት ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ከ150 ካሬ ሜትር የዓሣ ምርት እስከ 41 ሺህ ብር ገቢ እንደሚገኝ እና በሂደትም እንደሚጨምር ገልጸዋል። ዓሣን በኩሬ የማልማት አዋጭነት የተናገሩት ወይዘሮ ገነት መኖ ላይ በትኩረት ከተሠራ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ሰው በዘርፉ ላይ ቢሰማራ አትራፊ እንደሚኾንም መክረዋል።

በየጊዜው እያወጣን ከምንመገበው በተጨማሪ በአንድ የዓሣ ምርት ጊዜ (በስድስት ወር) እስከ 30 ኩንታል ዓሣ እናመርታለን ብለዋል፡፡ ዓሣ ማምረት ያልተለመደ በነበረባቸው እንደ ሰሜን ሸዋ እና ዋግ ኽምራ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የዓሣ ምርት እየተመረተ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አበበ አሁንም ግን ዘርፉ ትኩረት የሚያስፈልገው እንደኾነ ነው ያሳሰቡት።

የዓሣ ምርት እና ምግብ ዘግይቶም ቢኾን በሌማት ቱሩፋት መርሐ ግብር መካተቱን ጠቅሰው በሀገር ደረጃ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። የአማራ ክልልም በተለያዩ አማራጮች የተቀናጀ የዓሣ ልማት ፓኬጅ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል። አቶ አበበ የዓሣ ምርትን በተፈጥሮ የውኃ አካላት በዘላቂነት ለማስቀጠል፣ ንጽህናው የተጠበቀ ዓሣ ለማቅረብ፣ የድኅረ ምርት አያያዝ ላይ እና የምርት መሠብሠቢያ መሣሪያዎችን ተገቢ እና ዘመናዊ በማድረግ ላይ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉም ለማገዝ ዝግጁ ነን ብለዋል። ወይዘሮ ገነትም የዓሣ መኖን በራስ አቅም ማዘጋጀት እንደሚቻል ጠቅሰዋል። ከሌሎች የግብርና ዘርፎች ጋር በጥምር ሲሠራ ደግሞ የበለጠ ቀላል እንደሚኾን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሃይማኖት አባቶች የሰላም ሐኪም መኾን እንዳለባቸው ተጠቆመ።
Next articleየክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ የልማት ሥራዎችን ተመለከቱ።