ጥራት ያለው የሰብል ዘር ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው።

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተሻሻለው የዘር አዋጅ 1288/2015 ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል። በሕገ ወጥ ዘር ቁጥጥር ላይም ምክክር አድርጓል።

ሕገ ወጥ ዘር፣ ዝውውር እና አቅርቦት የሚባለው ትክክለኛ ያልኾነ ዘርን ጨምሮ ፈቃድ ሳይኖር ማምረት እና ማዘዋወር፣ ባልተገባ ሥፍራ ማከማቸት እና ማቅረብ እንዲኹም ባልተፈቀዱ ቦታዎች መገብየት ነው። ዘርን ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል፣ መንከር እንዲኹም ማሸጊያዎችን በመጠቀም አስመስሎ ማቅረብ በሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት የተፈረጁ ናቸው።

የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ዘላለም ልየው በሥራ ላይ ያለውን የዘር አዋጅ 1288/2015 ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት እየተሠበሠበ መኾኑን ገልጸዋል። አዋጁ ተሻሽሎ ሲጸድቅ ሕገ ወጥ የዘር ምርትን እና ችርቻሮን በመቆጣጠር እና ጠንካራ ተጠያቂነትንም በማስከተል የዘር ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል። በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንደሚኾን ተናግረዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤታቸው የሚመረትን ዘር በየደረጃው ቁጥጥር እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ ዘላለም በተሠሩ ሥራዎችም እስከ 5 ሺህ ኩንታል ጥራት የሌለው ምርጥ ዘር ውድቅ መደረጉን ጠቅሰዋል። ጥራት የሌለው ዘርን የሚያመርቱ እና የሚያከፋፍሉ ቢገኙ እስከ ፈቃድ መንጠቅ የሚደርስ ሥራ እንደሚሠራም ነው የጠቀሱት።

ዘር የሚያመርቱ፣ የሚያከፋፍሉ እና የሚቸረችሩ አካላት ሕጋዊነት እንደተጠበቀ ኾኖ ዘርን ከባዕድ ነገር ነጻ ማድረግ፣ መጠኑን ከመቀነስ፣ አመሳስሎ ከማቅረብ ነጻ መኾን አለባቸው ብለዋል። አጋር አካላት (ግብርና፣ ማኅበራት፣ ንግድ፣ ፖሊስ፣ ፍትሕ፣ ፍርድ ቤት እና ሌሎችም ተቋማት) የሕገ ወጥ ዘር ዝውውርን እና አቅርቦትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የመተባበር ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ደመቀ ወንዶች የፖሊስ ዋና ሥራው ወንጀልን መከላከል በመኾኑ የሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን የመከላከል፣ ሲገኝም ምርመራ አጣርቶ ለሕግ የማቅረብ እና ሌላውም እንዲማርበት እናደርጋለን ነው ያሉት። ከዚህ በፊት ሲሠራበት የነበረ በመኾኑ አኹንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያስገነዘቡት።

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ በውይይቱ ዘርን ከማምረት ጀምሮ እስከ መጨረሻ ተጠቃሚው ድረስ የሚኖረውን ግብይት እና ዝውውር ሕጋዊ ለማድረግ እና ወንጀሎችን ለመከላከል የጋራ ግንዛቤ መያዙን ገልጸዋል። ጥራቱ የተጠበቀ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በየደረጃው የሚገኘው የፍትሕ ተቋም መከላከልን ጨምሮ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር ተፈጽሞ ሲገኝ ለሕግ በማቅረብ አጥፊዎችን ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የዕጽዋት ዝርያ እና ዘር ሪጉላቶሪ መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ፍስሐ ተሾመ ውይይቱ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን የሚመለከተው አዋጅ የማስፈጸሚያ ደንብ እና መመሪያ ላይ በመወያየት ግልጽነት ለመያዝ መኾኑን ገልጸዋል። ሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት ሂደቱ ረጂም በመኾኑ የተለያዩ አካላት ተሳትፎ አለው። ይህም ለሕገ ወጥነት እንደሚያጋልጠው እና ችግሩን ለመከላከል ከሕግ አካላትም ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል።

ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት የግንዛቤ ፈጠራ እና የቁጥጥር ስልቶችን በመቀየስ ለመሥራት ዝግጅት መደረጉንም ነው አቶ ፍስሐ ያነሱት። አርሶ አደሮችን ጨምሮ በሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት በስምንት ክልሎች ላይ በተደረገ ጥናት በበቆሎ እና አትክልት ዘሮች ላይ ሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት የሰፋ መኾኑ ታይቷል ብለዋል። በቀጣይም የግብርና አደጋ መኾኑን አንስተዋል።

ያልተገቡ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ጉዳቱ በርካታ ስለኾነ ችግሩን ለማሳወቅ በመድረኮች እና በሁሉም አማራጮች የማሳወቅ ሥራም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር እና አቅርቦት በኅብረተሰቡ ዘንድ ግልጽነት ተፈጥሮበት ወንጀሉን መከላከል ይቻል ዘንድ የሚዲያ አካላትም የማሳወቅ ሥራ እንዲሠሩበት ነው የተጠየቀው።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕጻናት መብታቸው እስከ ምን ድረስ ነው?
Next articleየሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን ከተቀመጠለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።