
ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 36 መሠረት ሕጻናት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዳሏቸው እና ሕጋዊ ከለላ እንደተሰጣቸው በግልጽ ተቀምጧል። ሕጻናት እንደ ማንኛውም ተፈጥሯዊ ሰው መብት ያላቸው ሲኾን በሥነ አዕምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እና በአካላዊ ሁኔታ ምክንያት ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው በዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ ሕግ ማዕቀፎች ላይ ተደንግጓል፡፡
በዚህ መሠረትም ሕጻናት በሕይወት የመኖር መብት፣ ስምና ዜግነት የማግኘት መብት፣ ወላጆቹን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅ እና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት መብት፣ ጉልበት ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በጤናው እና በደኅንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፣ በትምህርት ቤቶች ወይም በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካል ላይ ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔ እና ኢ-ሰብዓዊ ከኾነ ቅጣት ነጻ የመኾን መብት እንዳላቸው በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል፡፡
በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ወይም በግል በጎ አድራጎት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአሥተዳደር ባለሥልጣኖች ወይም በሕግ አውጭ አካላት የሕጻናት ደኅንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡ ወጣት አጥፊዎች በማረሚያ ወይም በመቋቋሚያ ተቋሞች የሚገኙ በመንግሥት ርዳታ የሚያድጉ ወጣቶች በመንግሥት ወይም በግል እጓለ ማውታን ተቋሞች (የሕጻናት ማሳደጊያዎች) ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከአዋቂዎች ተለይተው መያዝ አለባቸው ይላል፡፡
እንዲሁም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ሕጻናት በጋብቻ ከተወለዱ ሕጻናት ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም መንግሥት ለእጓለ ማውታን ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እና በጉዲፈቻ የሚያድጉበት ሥርዓት የሚያመቻቹ እና የሚያስፋፉ፣ ደኅንነታቸውን እና ትምህርታቸውን የሚያራምዱ ተቋሞች እንዲመሠረቱ እንደሚያበረታታ ይደነግጋል፡፡
የሕጻንነት የሕግ ትርጓሜ መስጠትን አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የመብት እና ግዴታ ወሰንን ለማወቅ ስለሚያስችል ነው፡፡ ሌላው ሕጻናት ለአደጋ ተጋላጭ ከመኾናቸው አኳያ ልዩ ጥበቃ ስለ ሚያስፈልጋቸው ሕጻናትን በመለየት ጥበቃ ለማድረግ በማሰብ እንደኾነም በድንጋጌው ላይ ተጠቅሷል።
ሕጻን ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ትርጓሜዎችን አስቀምጠው ይገኛሉ። አንድ ወጥ የኾነ ትርጓሜ ባይኖርም እንኳ ሕጻን የሚለው ቃል ብዙ ሀገራት ዕድሜን ግምት ውስጥ ያስገባ ትርጉም ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በአንዳንድ ሀገሮች ሕጻን ለሚለው ትርጓሜ ለመስጠት ማኅበራዊ አረዳድን ግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ መረጃዎች ያሳያሉ። ለአብነት በጉርምስና ወቅት የሚታዩ አካላዊ ለውጦች እና የድምጽ መጎርነን ከግምት ውስጥ ሲያስገቡም የሚታዩ አሉ።
በዓለም አቀፍ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀፅ 1 ላይ ዕድሜን መሠረት ያደረገ ትርጉም ሲሰጥ ሕጻን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የኾነ የተፈጥሮ ሰው እንደኾነ ያትታል፡፡ ኾኖም በምን ጉዳይ እና ምን ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ዝቅ ማድረግ ወይም 18 ዓመት ሳይሞላ ለአካለ መጠን መድረስ እንደሚቻል ባያስቀምጥም ሀገራት በሚያወጡት ሕግ መሠረት ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች መውረድ የሚቻልበት አጋጣሚም እንዳለ በኮንቬንሽኑ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
በዚህ አግባብ ለአብነት በኢትዮጵያ ለጋብቻ ሲባል ማለትም ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ተጋቢዎቹ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው ወላጆች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ፍትሕ ሚኒስትሩ ከመደበኛ የጋብቻ እድሜ (18 ዓመት) ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ በሚኾንበት ጊዜ ሕጻኑ ከሞግዚት አሥተዳደር ነጻ እንደወጣ ይቆጠራል ይላል፡፡
በኮንቬንሽኑ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ከመወለድ በፊትም ማለትም በጽንስ ወቅትም ጥበቃ እንዳለ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ የሕጻናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 2 ሕጻን ለሚለው ትርጓሜ ሲሰጥ “ሕጻን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የኾነ የተፈጥሮ ሰው ነው” በሚል ነው።
ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጎች የሕጻናት መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማሰብ የተለያዩ መርሆችን አስቀምጠው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መርሆችም የሕጻናት መብቶችን ለማስከበር እና ለማስተግበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላሏቸው ነው፡፡ ከእነዚህ መርሆች ውስጥም ለሕጻናት ጥቅም እና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው መርህ ቅድሚያ ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ በ1959 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብት መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕጻናት ጥቅም እና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት የሚለውን መርህ አካቶ የወጣ ዓለም አቀፍ ሰነድ ኾኖ ይጠቀሳል፡፡ በመኾኑም ሕጻናት ነክ ውሳኔዎች ሲወሰኑ (ለምሳሌ ወላጆቻቸው የሚለያዩ ከኾነ ከማን ጋር መኖር እንዳለባቸው ሲወሰን) ውሳኔ ሰጭ አካላት ለሕጻናት ጥቅም እና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት የሕግ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ይላል፡፡
ከዚሁ በትይዩ ሌሎች መብቶችን ለማስፈጸም እና ለመተርጎም የሚያገለግሉ አራት መሠረታዊ ነጥቦችንም አካቶ ይገኛል፡፡ እነርሱም:- የእኩልነት መብት በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 2 ላይ፤ ለሕጻናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 3 ላይ፤ የመሳተፍ መብት በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 12 ላይ እና በሕይወት የመኖር እና በመልካም ሁኔታ የማደግ መብት በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 6 ላይ ተዘርዝረው የተቀመጡ ሌሎች ነጥቦች ናቸው፡፡
👉የእኩልነት መብት ሲባል በጾታ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ አቋም፣ በብሔር ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም አድሏዊ በኾነ በማንኛውም ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ልዩነቶች ሊደረጉ አይገባም በሚል የተቀመጠ ነው፡፡
👉ምግብ እና መጠለያ የማግኘት መብት:- ይህ በሕጉ ላይ ከተቀመጡ መሠረታዊ ነጥቦች ውስጥ አንዱ ነው። ሁሉም ልጆች ለትክክለኛው እድገታቸው አስፈላጊ የኾነውን ምግብ የማግኘት እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚኖሩበት ቤት የማግኘት እና የመደሰት መብት እንዳላቸው በግልጽ ተቀምጧል፡፡
👉የትምህርት የማግኘት መብት:- ልጆች ችሎታቸውን ለማዳበር እና የራሳቸውን የወደፊት ዕድል ለመፍጠር ትምህርት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ምክንያቱም ለትክክለኛው ሥነ-ልቦናዊ፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው አስፈላጊ እንደኾነም በሕጉ ተገልጿል፡፡
👉በጤንነት የማደግ መብት:- ይህ ነጥብ ልጆች ጤንነታቸውን ለመንከባከብ እና ለማቆየት እንዲሁም በሽታን ለመከላከል አስፈላጊ የሕክምና ክትትል እና እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው የሚያትት ነው። ወደ ጤናማ አዋቂዎች እንዲያድጉ መልካም ጤንነትን የማግኘት መብት እንዳላቸው የሚያስቀምጥ ነው፡፡
👉በሕይወት የመኖር መብት፡- ሕጻናት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች የመጠበቅ እና የመትረፍ መብታቸው የተጠበቀ እንዲኾን የሚገልጽ ነው። እንዲሁም በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት አላቸው ይላል፡፡
በአጠቃላይ ሕጻናት በተለይ በዕድሜያቸው ምክንያት ለተለያዩ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለኾነ ልዩ የኾነ ከለላ እና ጥበቃ የማግኘት መብታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ የሕጻናት መብት ሕጉ በዝርዝር ያስቀምጣል። ከዚህ በመነሳት የኛ ልጆች ከተቀመጠው ሕግ አንጻር ምን ያህል መብታቸውን እያከበርንላቸው ነው ? የሚለውን ለአንባቢ ይሁን እላለሁ።
በመረጃ ምንጭነት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን፣ ነጋሪት ጋዜጣን እና የፍትሕ ሚኒስቴር ድረ ገጽን ተጠቅመናል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን