
ጎንደር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራጭ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥነ ሥርዓቶችን ለማጎልበት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጁት መድረክ ላይ ተገልጿል። ምክክሩ በጎንደር ቀጣና ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው።
እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሽምግልና ሥርዓቶች እልባት እንዲያገኙ ሲሠራባቸው መቆየቱ ተገልጿል። አማራጭ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን ለማጎልበት አዋጅ ቁጥር 298/2017
በማውጣት ወደ ሥራ መግባቱን በአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት የሕግ ጥናት እና ምርምር ዋና የሥራ ሂደት መሪ አበበ ካሴ ነግረውናል። የአዋጁ መውጣት ከሽምግልና ሥርዓቱ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቶችን በመደገፍ ሰዎች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ አስፈላጊውን ፍርድ እንዲያገኙ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጥምረት እንደሚሠራም አቶ አበበ አስረድተዋል። ማኅበረሰቡ እንግልት ሳይገጥመው ባለበት አካባቢ ፍርድ እንዲያገኝ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር በጋራ
በመኾን እየሠሩ መኾናቸውን በውይይቱ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች አስታውቀዋል። የሽምግልና ሥርዓቱን በመደገፍ ለበርካታ ችግሮች መውጫ መንገድ አድርጎ መጠቀም እንደሚያስፈልግም የሀገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን