
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክረምቱን መግባት ተከትሎ በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የወባ በሽታ በወባ ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ከበሽተኛ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታ ነው። ትኩሳት፣ ቁርጥማት፣ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ እና ብርድ ብርድ ማለት የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው።
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የክልሉ የወባ ሥርጭት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። በክልሉ ከሐምሌ/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕሙማን ተመዝግበዋል ብለዋል። በበሽታው ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉንም ገልጸዋል።
በየሳምንቱ ደግሞ ከ22 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ እንደሚጠቁ ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ 40 ወረዳዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚኾነውን የክልሉን የወባ ሥርጭት ሽፋን እንደሚይዙ ገልጸዋል። አሁንም የዝናብ ሥርጭቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ሥርጭት ለመከላከል የወባ ኬሚካል ርጭት ይደረጋል ነው ያሉት። ከዚህም ባለፈ ከ4 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር ግዥ እንዲፈጸም መጠየቁን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም በቤቱ ውስጥ ያለውን የአልጋ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲሠራም አሳስበዋል። ምልክቶች ከታዩ ደግሞ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የጤና ተቋማትም በየሳምንቱ ሪፖርቱን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የሚገቡ የወባ መድኃኒቶችንም በጥንቃቄ መያዝ እና ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ሁሉም ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ወረዳዎችም ለወባ መከላከያ በጀት በመመደብ የመከላከል ሥራው ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን