
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምት መግባትን ተከትሎ በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ ሰጥቷል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ኮሌራ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ መኾኑን ገልጸዋል።
በሽታው ሲከሰት አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል የሰውነትን ፈሳሽ አሟጦ ያስወጣል፣ አፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገ ደግሞ አቅምን በማዳከም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ መኾኑን ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ የኮሌራ በሽታ በክልሉ በተለያዩ ዓመታት ተከስቶ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም ከታኅሣሥ 23/24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 316 በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች ሕክምና አግኝተዋል ብለዋል። በሽታው ሕይዎትን የሚቀጥፍ እንደኾነም ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ሳምንታት ሰባት ወረዳዎች ሪፖርት ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት። ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ደራ፣ ቋራ፣ ጃዊ እና ቡሬ ወረዳዎች ተጠቃሾች ናቸው ነው ያሉት። በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ከዚህም ባለፈ ሕሙማንን መለየት እና በፍጥነት ማከም፣ የጉዞ ወኪሎችን ወደ ጸበል ቦታ የሚያደርጉትን ጉዞ ለተወሰነ ጊዜ መግታት እና በተቻለ መጠን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ማቅረብ በመቻሉ የበሽታውን ሥርጭት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
ይሁን እንጅ አሁንም በሽታው የተከሰተባቸው አንዳንድ የጸበል ቦታዎች ካላቸው ርቀት አኳያ ተጓዦችን ሙሉ በሙሉ መግታት ባለመቻሉ፤ የመጸዳጃ ቤቶችን በተሟላ መንገድ መገንባት ባለመቻሉ፤ በተገነቡ መጸዳጃ ቤቶችም በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ እና ሙሉ በሙሉ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ባለመቅረቡ ሥርጭቱን ዜሮ ማድረግ አለመቻሉን ነው የተናገሩት።
አሁንም የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ ሕዝብ ይሰበሰብባቸዋል የተባሉ ከ54 በላይ የጸበል ቦታዎች መለየቱንም ገልጸዋል። ከእነዚ ውስጥ ደግሞ ይበልጥ ሥጋት ያለባቸው ናቸው ተብለው በተለዩ 22 የጸበል ቦታዎች የጤና ባለሙያዎች ተመድበው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በሽታውን ለመከላከል ማኅበረሰቡ ንጹሕ መጠጥ ውኃ መጠቀም፤ የንጹሕ መጠጥ ውኃ በሌለበት አካባቢ ደግሞ ውኃን አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም በውኃ ማከሚያ ኬሚካል አክሞ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። የምግብ ንጽሕናን መጠበቅ፤ ምግብን በሚገባ አብስሎ እና በትኩስነቱ መመገብ ይገባልም ብለዋል። መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም፤ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እና ምግብ ከማዘጋጀት እና ከመመገብ በፊት እጅን በአግባቡ መታጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምልክቶቹ ከታዩ ደግሞ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ሕክምና ማግኘት ይገባል ብለዋል። በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሌሎች ተቋማትም ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
