
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከግንቦት 19 እስከ ግንቦት 28/2017 ዓ.ም የሚከበረውን የአካባቢ ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጋሻው እሸቱ “የፕላስቲክ ብክለትን እንከላከል” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረውን የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን በአማራ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ብለዋል።
የዓለም የአካባቢ ቀን መከበር የጀመረው በ1964 ዓ.ም በስዊዘርላንድ መኾኑን ጠቅሰዋል። የበዓሉ መከበር ዋነኛ ዓላማም ዓለማችን ቀስ በቀስ ወደብክለት እየገባች መኾኑን በመገንዘብ ሰዎች ሁሉ ለአካባቢ ጥበቃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው ብለዋል። የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ52ኛ በኮሪያ ሪፐብሊክ ይከበራል። ቀኑ በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ፣ እንደ አማራ ክልል ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
በአማራ ክልል ለማክበር በርካታ የግንዛቤ ፈጠራ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል። በተለይም ዋነኛ የአካባቢ በካይ የኾነውን የፕላስቲክ ምርት ከመጠቀም መቆጠብ፤ ከተጠቀምን ደግሞ ጤናማ የአወጋገድ ዘዴ መከተል እንደሚገባ ግንዛቤ የመፍጠር ንቅናቄ ይካሄዳል ነው ያሉት። ፕላስቲክ መሬት ላይ ከወደቀ በኃላ በቶሎ ስለማይበሰብስ ዋነኛ አካባቢን በካይ ነው፤ እንስሳትንም እየገደለ ነው፤ ለሰው ልጆችም ጤና ጠንቅ የኾነ ቁስ ነው ብለዋል።
በመኾኑም የሰው ልጆች ሁሉ የፕላስቲክ ምርቶችን በመተው እንደጨርቅ አይነት ያሉ በቀላሉ በስብሰው ከአፈር ጋር የሚዋሀዱ ቁሶችን መጠቀም ይገባቸዋል ነው ያሉት። “ለአካባቢ ብክለት ምክንያት የኾኑ የፕላስቲክ ምርቶችን ከመጠቀም ባሕል በመውጣት ለምድራችን ጤና አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን” ብለዋል በመልዕክታቸው።
በርካታ ሀገራት የፕላስቲክ ከረጢቶች ከመጠቀም ባሕል ወጥተዋል ያሉት አቶ ጋሻው በኛም ሀገር የፕላስቲክ ከረጢቶች በጨርቅ ከረጢቶች መተካት እንዳለባቸው አመላክተዋል። ፕላስቲክ በሰዎች፣ በእንስሳት እና በብዝኀ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ፣ በሥነ ምኅዳር ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ መኾኑንም ተናግረዋል።
ፕላስቲክን በየቦታው ከመጣል መቆጠብ፣ ይልቁንም በአግባቡ መያዝ እና ወደፋብሪካዎች በማስገባት እንደገና መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን 52ኛውን የዓለም የአካባቢ ቀን ሲያከብር ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የተለያዩ ሁነቶችን እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።
በዓሉን ከግንቦት 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ በፓናል ውይይት፣ በጽዳት ዘመቻዎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ በሚያስችሉ ተግባራት እና ባለድርሻ አካላትን በሚያሳትፉ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል። ቀኑ በዞኖች፣ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች ደረጃ ይከበራል፤ ግንቦት 28/2017 ዓ.ም ደግሞ ክልል አቀፍ የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ይከናወናል ብለዋል።
የአካባቢ ብክለት ጉዳት በቶሎ የሚታወቅ አይደለም፤ ይልቁንም ቀስ በቀስ የሰውን ልጆችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ ስለዚህ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለትውልድም ጤና በማሰብ አካባቢውን ማጽዳት አለበት ነው ያሉት። በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን መጠነ ሰፊ የፕላስቲክ ብክለት በጋራ በመሥራት መቅረፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን