
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሕጻናት የኩፍኝ በሽታ ክትባት በዘመቻ መስጠት መጀመሩ ይታወሳል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ክፍል አስተባባሪ ተሰማ በሬ ከግንቦት 06/2017 ዓ.ም እስከ ግንቦት 15 /2017 ዓ.ም የኩፍኝ በሽታ ክትባትን በዘመቻ መልክ በክልሉ 175 ወረዳዎች በ4ሺህ 138 ቀበሌዎች ተደራሽ መኾኑን ገልጸዋል።
በዘመቻው ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ ታቅዶ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መከተባቸውን ተናግረዋል። የክትባት ዘመቻው እንደ ክልል 95 በመቶ የሚኾነው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡
ኅብረተሰቡ የክትባቱን ጥቅም በመረዳት ልጆቹን ለማስከተብ ያደረገው ርብርብ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚዲያ ሽፋን መኖሩ፣ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ፣ የክትባት መድኃኒቱ በየመከተቢያ ጣቢያዎች ቀድሞ ተደራሽ መኾናቸው እና የባለሙያዎች ቅንጅታዊ አሠራር የክትባት ዘመቻው ውጤታማ እንዲኾን እንዳስቻሉት ነው ያብራሩት፡፡
የኩፍኝ በሽታ ለዐይነ ስውርነት፣ ለጀሮ ሕመም እንደሚያጋልጥ እና ለሞት የሚዳርግ በሽታ መኾኑንም ገልጸዋል። የክትባት ዘመቻውም ሕጻናት በኩፍኝ በሽታ እንዳይያዙ፣ በበሽታው ምክንያት ለዐይነ ስውርነት እንዳይዳረጉ እና በበሽታው ምክንያት የሚመጣውን ሞት ለመቀነስ የተሰጠ ክትባት ነው፡፡ በቀሪ ጊዜያት መደበኛ ክትባቶች እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
ከኩፍኝ ክትባት ዘመቻው ጎን ለጎን በቅንጅት ለመሥራት በተደረገው ጥረት 9ሺ 292 የሚኾኑ በማሕጸን በሽታ የተቸገሩ እናቶች፣ 11ሺህ 144 የሚኾኑ የታመሙ ሕጻናት፣ 128 በተፈጥሮ የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ የገጠማቸው ሕጻናት፣ 189 በተፈጥሮ እግራቸው ችግር ኖሮባቸው የተወለዱ ሕጻናት የልየታ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዘመቻው የሥርዓተ ምግብ ልየታም ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የልየታ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ዘመቻው ሰፊ ጥቅሞች የተገኙበት መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን