
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ መዳረሻ ለመሆን እየሠራች መኾኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት 51ኛውን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፈረንስ እና ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ አስጀምረናል ብለዋል።
ጉባኤው ከ93 የአፍሪካና የሌሎች የዓለም ክፍላተ ሀገራት የመጡ የኢንሸራንስ ተቆጣጣሪዎች፣ የመድን አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና የዘርፍ ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ ኢንሹራንስ መጠናከር ስልት የሚቀይሱበት መኾኑን አመላክተዋል። በአፍሪካ ያለው የኢንሹራንስ አሠራር መሻሻል አለበት፥ ዘርፉን የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ለፈጠራ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ንግድን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ስርዓት እየተገነባ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ ቁልፍ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል።
የኢንሹራንስ ዘርፉ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ ማዕከል በመሆኑ ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው፤ ለአብነትም ፈጠራን ለማሳደግ፣ ውጤታማ ቁጥጥርን ለማጠናከርና የፖሊሲ ባለቤቶችን ለመከላከል ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አቋቁመናል ነው ያሉት።
በቅርቡ መንግሥት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አጠቃቀም እና ባለቤትነትን በተመለከተ አዲስ ሕግ ማዘጋጀቱ በቤት ልማት በመሠረተ ልማት እና በሪል ስቴት ዘርፍ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ አቅሞችን የሚያሳድግ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተስፋ የሚጣልባት የኢንሹራንስ ገበያ ለመሆን እየሠራች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን