
የታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ በቅረቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸው ይታወሳል። እነዚህን ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚገመግም በፌዴራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአሃዱ ቲቬ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል። አብመድም መረጃው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው ነው ያሉት ኃላፊው ጉዳዩን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ መረጃውን ደረጃ በደረጃ መስጠት በሚገባ መልኩ ለመስጠት ቃል ብንገባም ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ብለዋል።
ጉዳዩ ውስብስብ ከመሆኑም በላይ በጉዳዩ ዘንድ ቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ብለዋል አቶ ንጉሱ። ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 28 ሰዎች መያዛቸውንም በመግለጽ።
ለዚህም በማኅበራዊ ድረ ገጽ የተሳሳተና ያልሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ እየደረሰው ነው ያሉት አቶ ንጉሱ “ታግቼ ነበር ተማሪ ነበርኩ ”ብለው በተለያየ መልኩ የቀረቡ ወደ 4 ያህል ተማሪዎች እንደተያዙ ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማድበስበስ የሞከሩም ተይዘዋል ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ግብረ ሃይል ስራውን ሌት ተቀን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸውም ዝርዝርና የተሟላ መረጃውን በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።
አቶ ንጉሱ “እገታው እንዲከሰት ያቀዱ፣ ያቀነባበሩ መረጃ የሰጡና ያሰማሩ የተለያዩ ወገኖች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገላቸው ነው” ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ጉዳዩን በማድበስበስ ሌላ መልክ እንዲይዝ በማድረግ በሰፊው እየሰሩ ያሉ ሰዎችና ግለሰቦችም አሉ፤ ጉዳዩን በመደበኛ መረጃ ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ ሲጠናቀቅ ዝርዝሩ ለኅብረተሰቡ ይሰጣል ብለዋል።
ጉዳዩ በርካታ አካባቢዎችንና አካላትን አነካክቷል ያሉት አቶ ንጉሱ “የአማራ ክልላዊ መንግስታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፌዴራል ጋር ሆነው እየሰሩ ነው” ብለዋል። በከፊልም ከቤንሻንጉል ክልል የሚያገናኘው ነገርም ስላለ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የፌዴራል ግብረ ሃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ 24ኛ ክፍለ ጦርና ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በመሆን ቀደም ብለው በህዳር 25 ተይዘው የነበሩ የአካባቢው ወጣቶች፣ አንዳንድ አመራሮችና እነዚሁ 21 ተማሪዎች ተለቅቀው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና የከተማዋ ከንቲባ ባሉበት ወደ ዩኒቨርሲቲው መልሰው ከዚያ በኋላ ሌሎች ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች ወጥተው የነበረ መሆኑን በሰነድም በቦታው ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል።
በጥቅሉ ሁኔታው የብዙ አካላት ዕጅ ያለበት መሆኑ፣ እጅግ ውስብስብ እንዲሁም በጉዳዩ የሚካሄደው ፍተሻ እንዳይሳካ እግር በእግር በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራበት ቢሆንም አስፈላጊውን መረጃ እየተሰበሰበ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በየጊዜው ከሚመጡ መረጃዎችም ልጆች ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳይ አንዳችም መረጃ የለም ብለዋል አቶ ንጉሱ።
መንግስት መስራት ያለበትን ስራ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ መረጃዎች ተሰብስበው ሲጠናቀቁ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።