
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ከጢስ ዓባይ ቀጣና ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የጥንት ጀግኖች አባቶቻችንን የክብር ሥም ይዞ ነገር ግን ይህንን ስም በማይመጥን ተራ የዝርፊያ ተግባር ላይ የተሰማራ ቡድን ሕዝብን እያደናገረ ክልሉንም ለማመሰቃቀል ሲጥር ቆይቷል ብለዋል።
የጢስ ዓባይ እና አካባቢው ማኅበረሰብም ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ በገዛ ልጆቹ ዋጋ ሲከፍል መቆየቱን ገልጸዋል።
ታጣቂዎች በቀላሉ አስተምረን የማንተካቸውን ዶክተሮች አሳጥተውናል፤ ትውልድ የሚቀርጹ መምህራንን በማሳደድ የልጆችን ትምህርት ዘግተዋል፤ ሕጻናት የሰፈር ታጣቂዎችን በማየት እና አጉል ልምድ በመቅሰም ቀለም በሚለዩበት ዕድሜያቸው የእንጨት ጠመንጃ ለመሸከም ዳድተዋል ነው ያሉት። ከዚህ በላይ የከፋ የትውልድ ሳንካ የለምና ከልብ መወያየት እና ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ግድ ይላል ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየሞተም ቢኾን ሕዝብን ሲጠብቅ፣ ሰላሙንም ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አንስተዋል። ይህም ጥረት ፍሬ አፍርቶ ክልሉ ሰላም አግኝቷል፤ ሕዝቡም ወደ ልማቱ እንዲገባ አስችሏል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቢኾን በየጫካው የሚሹለከለኩ እና ጨለማን ተገን እያደረጉ ሕዝብን የሚበድሉ ታጣቂዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል።
መንግሥት ሁሌም ቢኾን ለሰላም በሩ ክፍት ነው፤ ሰላምን የሚመርጡ ታጣቂዎችንም በክብር ተቀብሎ እንዲያለሙ ዕድል እየሰጠ ነው ብለዋል። ይህም የመንግሥትን የሰላም ቁርጠኝነት በተግባር ያስመሰከረ ስለመኾኑ አንስተዋል።
እስካሁን የደረሰውን ጥፋት አውግዘን እንተው፤ እንዳይደገም ግን በጋራ እንሥራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
ሰላምን የማይፈልግ እና ሕዝብን እየበደለ የመቀጠል አባዜ ያለበትን ታጣቂ ቡድን ከሕዝብ ጋር በመኾን ተከታትለን እንይዛለን፤ ለሕግም እናቀርባለን ብለዋል።
ከዚህ በኋላ የሕዝብን ጥያቄ ለማስመለስ በማስመሰል ታጥቆ ማደናገር፣ የራስን ሕዝብ መበደል፣ እንዳይሠራ መከልከል፣ እንዳይነግድ መንገድ መዝጋት እና የአገልጋይ ልጆቹን ደም ማፍሰስ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት። በተጠናከረ ሕግ የማስከበር ርምጃም እናስቆመዋለን ሲሉም ተናግረዋል።
የጢስ ዓባይ ከተማ ነዋሪዎች ያለባቸውን የንጹህ መጠጥ ውኃ፤ የመብራት መቆራረጥ እና ሌሎችንም የልማት ጥያቄዎች ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት ይዞ እንደሚፈታም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።
ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው፤ የመንግሥት ሠራተኞችም ከተማ አሥተዳደሩ በሚዘረጋው ሥርዓት መሠረት ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ከንቲባው ተናግረዋል።
ሕዝቡ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን ለአካባቢው ሰላም መኾን መሥራት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አካባቢው ወደ ተሟላ ሰላም እንደተመለሰ ከጢስ ዓባይ እስከ ባሕር ዳር ያለውን አስፋልት መንገድ ግንባታ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንደሚገባም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ ተናግረዋል።
“የባሕር ዳር ከተማ ምልክት እና የቱሪዝም ስበት ለኾነው የጢስ ዓባይ አካባቢ ሰላም እና ልማት ያለመታከት እንሠራለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ እንዲኾን ቀዳሚው ነገር ሰላም ነው፤ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቁም ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን