
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” የኢንቨስትመንት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና በከተማዋ እያለሙ የሚገኙ አልሚ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡ በከተማዋ በአምራች ዘርፉ ብቻ 745 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።
ከዚህ ውስጥ 140ዎቹ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ምርት ሂደት ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው ተብሏል።
130 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ምርት ማምረት የጀመሩ መኾናቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናግረዋል፡፡
157 የሚኾኑ ፋባሪካዎች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ መኾናቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹ 318 ፋብሪካዎችም ቅደመ ግንባታ ሂደት ላይ ናቸው ተብሏል።
ከአምራች ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በከተማዋ 233 የአገልግሎት እንዲሁም 33 የከተማ ግብርና ዘርፎች ላይ ስምሪት የወሰዱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አቶ በድሉ አስታውሰዋል፡፡
በጥቅሉ በከተማዋ 145 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ፣ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን