
እንጅባራ: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ” የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት”በሚል መሪ መልዕክት ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከተለያዩ የጤና ተቋማት ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ጫና ያገናዘበ የደመወዝ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የጤና መድኅን ሽፋን እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የባለሙያዎችን የጥቅማጥቅም ጥያቄ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ግን አግባብ እንዳልኾነም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
በጤና ተቋማት ለአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት የኾኑ የሕክምና ግብዓቶች እና የመሠረተ ልማት ችግሮችም ሊፈቱ እንደሚገባ አንስተዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው የጤና ባለሙያዎች ባለፉት ዓመታት በበርካታ ጫና ውስጥ ኾነው የገቡትን ቃል በተግባር እየተወጡ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች የሚጠይቋቸው ውለው ያደሩ ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱት ኀላፊው ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎችን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ግን ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
የመብት ጥያቄዎች የሚቀርቡት ሥራን በሚበድል እና ህሙማንን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መኾን እንደሌለበትም ነው ያስረዱት።
መንግሥት ለባለሙያዎች ጥያቄ የሀገሪቱን የመክፈል አቅምን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን