
“መሬት ፈላጊ ውሸቶች”
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝቧ “አማኝ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ የሚጣረሱ በርካታ ጉዳዮች በራሷ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እየታዩ መኾናቸውን ብዙውን ጊዜ አስተውላለሁ፡፡ ለአብነት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች በሰዎች ላይ በተለይም ዕድሜያቸው ገፋ ባሉ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ሰብዓዊነት የጎደላቸው ማሰቃየቶች እና ግድያዎች ኢትዮጵያን የአማኝ ሀገር እንደነበረች እንጂ እንዳልኾነች ለማሳየት በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
በየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮት ሀሰት የኃጢአት ምንጭ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሀገራችን ውስጥ “ዋሽቶ ማስታረቅ” ሳይኾን “ዋሽቶ መስረቅ” እየተለመደ ይመስላል፡፡
ለዚህ ትዝብቴ መነሻ የኾነኝ በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለጸጥታ ዓባላት እና ለጡረተኞች የቤት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥ የከተማ አሥተዳደሩ ቃል መግባቱን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ የነገሰው ውሸት “እውነት ድሮ ቀረች” እንድንል እያስገደደን ነው፡፡
በተለያየ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ባለትዳሮች የቤት መሥሪያ ቦታ የመሰጠት ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ በሀሰት ፍቺ ውስጥ መዳከራቸው ምን ያኽል ከዕምነታችን ለመራቃችን ማሳያ ነው፡፡
ይኼው የቦታ ጉዳይ ከመነሳቱ በፊት ጋብቻ ሲመሠርቱ በግል ቤታቸው የጠሩን፣ በልጆቻቸው ክርስትና ላይ ተገኝተን ለፍሬ ይብቁላችሁ ያልናቸው፣ የልጆቻቸውን ልደት በጋራ አክብረን ለሠርጋቸው ያብቃን ያልናቸው ባለትዳሮች ትዳር የለንም ሲሉ ይስታዋላል፡፡ የውሸት ማስረጃ ማያያዝ ኢትዮጵያውያን ከሀቅ ጋር ምን ያኽል እንደተፋታን እና ከመልካም እሴታችን እንደራቅን የሚያሳይ ነው፡፡
ባል ወይም ሚስት ከዚህ ቀደም ባገኙት የቤት መሥሪያ ቦታ ላይ እንደ አቅማቸው ቤት ገንብተው፣ በቤታቸው በመገኘት “ቤት ለእንቦሳ” ስንላቸው “እንቦሳ እሰሩ” ያሉን ባለትዳር ወዳጆቻችን ቤት የለንም ወይም ተፋትተናል ይስታዋላል። የኛ መታዘብ ቁም ነገር ባይመስላቸው እንኳን በውሸት ትዳራቸውን ማፍረሳቸው የእውነት ቢሆንስ ብለው አያሰጋቸውም?
ባል እና ሚስት በሁለቱም ስም የቤት መሥሪያ ቦታ አግኝተው አንደኛውን ቦታ በመሸጥ በቀሪው ቦታቸው ላይ ቤታቸውን ለመሥራት ማሰባቸው ክፉ ሀሳብ ላይኾን ይችላል፤ ሃሳባቸው ክፉ የሚኾነው ትዳር መሥርተው አንድም ቦታ ያላገኙ ዜጎች መኖራቸውን እያወቁ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳ ዓይነት ራስ ወዳድ መኾናቸው ነው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቤት መሥሪያ ቦታ ለሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ያዘጋጀውን መልካም ዕድል እንደ ከዚኽ ቀደሙ ኹሉ የመሬት ደላሎች እንዳይቀራመቱት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አንድ ሰው በተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች ተጠቅሞ ብዙ ቦታዎችን እየወሰደ ቸብችቦ የግፍ ሀብታም ሲኾን ከዚኽ በፊትም ዓይተናልና፡፡
ከሁሉም በላይ ትዳር ላለው ሰው ትዳር የለውም ብለው የሚመሰክሩ ከህሊናቸው የተጣሉ ሰዎች ስለ ብዙዎች ችግር ሲሉ ከህሊናቸው እንዲታረቁ መምከርም ግድ ይለናል፡፡
የሀሰት ፍቺን የሚያጸኑ የሃይማኖት ተቋማት፣ የቀበሌ ፍርድ ሸንጎዎች እና የመንግሥት የፍትሕ ተቋማትም በብዙ ችግረኞች ዕድል ላይ ስለሚወስኑት ሃቅ ላይ ያልተመሠረተ ውሳኔ ደጋግመው እንዲያጤኑ ማሳሰብም ሚዛናዊነት ነው፡፡
በቀጣይ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስመለስ፣ ፍቺን የተመለከቱ የሀሰት ማስረጃ ስለሚሰጡ የቀበሌ ሹመኞች፣ የሀሰት የነዋሪነት መታወቂያ በገንዘብ ስለሚቸበችቡ ግለሰቦች፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ቅድሚያ ለባለትዳሮች ይሰጥ ይኾናል በሚል መላ ምት የሀሰት ጋብቻ ስለሚፈጽሙና ስለሚያስፈጽሙ ሰዎች እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የከተማ አሥተዳደሩን በምን መልኩ ቢያግዙ የታቀደው ቦታ ለትክክለኛ ሰዎች እንደሚደርስም ሃሳቤን ከትዝብቴ ጋር አዳብዬ አጋራለሁኝ፡፡
እናንተም በዚሁ የአሚኮ ዲጂታል ገጽ ሀሳብ እና አስተያየታችሁን እያጋራችሁ የእውነት ክር ምን ያኽል ብትቀጥንም እንደማትበጠስ ማሳያ ትሆኑ ዘንድ ጋብዘናችኋል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን