ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ተግባርን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

73

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራትን በተመለከተ በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ክልላዊ የሥልጠና መድረክ እያካሄደ ነው።

በኮሚሽኑ የሲስተም አሥተዳደር ከፍተኛ ባለሙያው ወሰን ደረጀ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ምንነት፣ መከላከል እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሥልጠና ሰነድ አቅርበዋል።

የሥልጠናው ዓላማም በሁሉም የክልሉ ተቋማት ያሉ ሠራተኞች እና ተሿሚዎች የትምህርት ሰነድ አግባብነት ባለው ተቋም ማጣራት እንደኾነ ጠቅሰዋል።

በሂደቱም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በክልሉ እየሠሩ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች እና ተሿሚዎች ከተገኙም ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል በክልሉ የመንግሥት ተቋማት እየሠሩ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችን እና ተሿሚዎችን የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃን ማጣራት አንዱ ነው።

በዚህ ረገድ እስከ ወረዳ ባሉ የተቋማት አደረጃጀቶች ውጤታማ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ተጠቅሞ ቅጥር መፈጸም፣ የደረጃ ዕድገት እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማስከበር ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ከፍተኛ ባለሙያው አብራርተዋል።

ጉዳዩ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ እንደዚኹም የሕዝብን መብት እና ጥቅም የሚያሳጣ መኾኑም ተነስቷል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በረቀቀ መልኩ የሚዘጋጅ፣ በትክክል የተማሩትን ዜጎች ዋጋ የሚያስከፍል፣ አገልግሎት አሰጣጥን አደጋ ላይ የሚጥል እንደኾነም ተጠቅሷል።

በራሱ የሚተማመን፣ ታታሪ እና ብቁ ሠራተኛ እንዳይፈጠርም ተጽዕኖው የጎላ እንደኾነ ነው የተነሳው።

በመማር ዕውቀትን የማዳበር ተስፋ ያላቸውን ዜጎችም ተስፋ ያስቆርጣል ብለዋል በማብራሪያቸው።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ ያሉ ችግሮችን እንደሚያስቀር ታምኖበት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።

ሥራውን በጥራት ለማከናወን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ርብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን የዕቅድ፣ በጀት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር በቀለ በለጠ በሰጡት ማብራሪያም የመንግሥት ዕቅድ ስኬታማ እንዲኾን በሥልጠናው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልጋል።

በሥልጠና መድረኩ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ከደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳር፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በኢትዮጵያ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተካሄደ ነው” አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)
Next article“መሬት ፈላጊ ውሸቶች”