
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት የኢንቨስትመንት መድረክ በደብረብርሃን ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋና ዓላማው በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ነው ብለዋል።
ከዘልማድ አሠራር በመውጣት የዘመነ እና የተቀላጠፈ የሥራ ባሕል ለማምጣት እንደዚህ አይነት ንቅናቄዎች ወሳኝ ናቸው ነው ያሉት።
የአምራች ኢንዳስትሪው በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጅ ሽግግር እና የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ መንግሥት በቀጣይ ዓመታት የሚተገበር መሠረታዊ የለውጥ ዕቅድ ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ደብረብርሃንን ማዕከል ያደረገ የኢንዳስትሪ ዞን እየተገነባ ነው ያሉት ዶክተር አህመዲን ይህንን መሠረት በማድረግም እንደ ከተማም እንደ ቀጣናም ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች መዳረሻ እንድትኾን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የአምራች ኢንዱስትሪን የሚያነቃቃ እንደ ኢትዮጵያ ታምርት አይነት ንቅናቄ ብዙ ሀገራት የሚጠቀሙበት የልማት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ምርት ሳይገቡ የቆዩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ተግባር እንዲገቡ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ደረጃ ባለፉት ወራት በርካታ ችግሮች የነበሩ ቢኾንም 288 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው ተስተናግደዋል ብለዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ 151 ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትልቁን ሚና እንደተጫወተም አስረድተዋል።
በዘርፉ የአምራች ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት የፋይናንስ እና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ማነቆ ቢኾኑም ከስር ከስር ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማዋ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
በከተማዋ ያለሙ ባለሀብቶች ከአሥተዳደሩ ጋር በቅርበት መሥራት በመቻላቸው ከግንባታ አልፎ ወደ ምርት መሸጋገር እንዲችሉ ኾኗል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመት ብቻ 25 የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ሲኾን ከ130 በላይ ኢንዱስትሪዎች በማምረት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በመለዬት መፍትሄ ለመስጠት ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ ስለመኾኑም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን