3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልል መድረሱን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

23

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለአሚኮ እንዳሉት 4 ነጥብ 1ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የአማራ ክልል ድርሻ ወደብ ላይ ደርሷል።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው አያይዘውም 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ መድረሱን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

ቀሪው ማዳበሪያም እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ተጓጉዞ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ነው አቶ አጀበ የተናገሩት።

መንግሥት በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይኖር ቀድም ብሎ ውል ተይዞ የተገዛ መኾኑን አቶ አጀበ ተናግረዋል። በዋጋ ረገድ ግን ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በመጨመሩ ነው።

መንግሥት እንደ ሀገር 87 ቢሊዮን ብር የአፈር ማዳበሪያ ድጎማ ማድረጉን አቶ አጀበ አስታውሰዋል። ይህም እያንዳንዱ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺህ 700 ብር እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ነዋሪው አርሶ አደር አምሳሉ ጋሸዬ የአፈር ማዳበሪያ በሚፈልጉት ልክ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል። ዋጋው ባለፈው ዓመት ከገዙበት መጨመሩንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ለ2017/18 የመኽር ምርት የሚኾን 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስታውሰዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ መሪዎች ከጢስ ዓባይ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next article“በኢትዮጵያ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተካሄደ ነው” አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)