
በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች “ጥያቄያችን ይመለስልን” የሚሉ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ሰልፎቹ የክልሉ መንግስትን ምላሽ የሚፈልጉ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነገቡ መሆናቸውን በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች መናገራቸውን ፋብኮ ዘግቧል።
በሽሬ እንደስላሴ እና አካበቢው እንዲሁም በዋጅራት አካባቢ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር፣ የመሰረተ ልማት እንዲሁም ከስራ ዕድል ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።
በተለይም በሽረ እንደስላሴ አካበቢ አስተያዬት የሰጡ ነዋሪዎች በወረዳ የመደራጀትና የወረዳ ዋና ከተማ ከመሆን ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ቢነሱም የክልሉ መንግስት አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ተናግረዋል።
በክልሉ እስከታች ቀበሌ ድረስ ስልጣን በ”ኔትዎርክ” ትስስር የሚሰጥ እንደሆነና ሕዝቡን የሚጠቅሙ ስራዎችም እየተሰሩ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ለዓመታት ሲነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችም አሁንም ድረስ አለመመለሳቸውን፤ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ ወጣቶች የስራ ዕድል ጥያቄ ቢያነሱም ያን የመመለስ ፍላጎት በክልሉ መንግስት ዘንድ አለመኖሩን ነው የተናገሩት።
በተለይም በሽረ እንደስላሴ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤት ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥም እስካሁን ወደ ግንባታ አለመገባቱን ነዋሪዎቹ አንስተዋል። ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ደግሞ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚውል 20 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገቢ መደረጉን አረጋግጧል። ግንባታው በክልሉ መንግስት መካሄድ ቢኖርበትም እስካሁን ግንባታው አለመከናወኑንም የከተማው ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
ወጣቶች መሰል የስራ ዕድል ጥያቄዎችና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ሲያነሱም ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “የትግራይን አንድነት ከማይፈልጉ እና ከትግራይ ጠላቶች ጋር እየሰራችሁ ነው፤ ባንዳ ናችሁ” የሚሉ እና ሌሎች ፍረጃዎች እንዳሉ በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉት ተናግረዋል።
ሰልፎቹ በሰላማዊ መልኩ መካሄዳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ በክልሉ መንግስት ዘንድ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የማስፈራራት አዝማሚያ መኖሩንም ጠቁመዋል። የክልሉ መንግስት ነዋሪዎቹ ለሚያነሷቸው ረጅም ዓመታት ለፈጁ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነም የፌዴራል መንግስት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያሰጣቸው ጠይቀዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ስለተካሄዱት ሰልፎችም ሆነ እየተነሱ ስላሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በስልክ የተደረገ ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ አብመድ ሀሳቡን ለማስተናገድ ዝግጁ ነው።