
👉”የመጀመሪያው ክልላዊ ራዲዮ”
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የራሱ የራዲዮ ጣቢያ እንዲኖረው የአማራ ክልል ምክር ቤቱ የወሰነው 1986 ዓ.ም ነበር።
የኢትዮጵያ የብዙኃን መገናኛ ዕድገት በሚል ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ያሳተሙት መጽሐፍ እንደሚያትተው ውሳኔውን የክልሉ ምክር ቤት ቢወስንም በወቅቱ ይህን ሊሠራ የሚችል አቅም ባለመኖሩ ዕቅዱ ለመዘግየት ተገድዷል።
በመጨረሻም ጣቢያውን ለማቋቋም የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ተገኝቶ በዚህ ሳምንት ግንቦት 16/1989 ራዲዮ ጣቢያው መደመጥ ጀምሯል።
የራዲዮ ጣቢያው ለአማራ ሕዝብ ድምጽ በመኾን ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ራዲዮ ጣቢያው ሥራ የጀመረው ከኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ጣቢያ የአየር ሰዓት ወስዶ በመሥራት ነበር።
የአማራ ራዲዮ ሲጀምር 14 ሰዎች ተቀጥረውለት ነበር ጣቢያው ሥራ እንዲጀምር የተደረገው።
ከሚያዝያ 16/1986 እስከ ግንቦት 15/1986 ድረስ ዋናውን መርሐግብር አየር ላይ ከማዋሉ አስቀድሞም የሙከራ ስርጭት አካሂዷል።
👉የአፍሪካ ኅብረት ምስረታ
በመጀመሪያ መጠሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት በሚል ስያሜውን የለወጠው ድርጅት የተመሠረተው ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ነበር::
ለምሥረታው ዕውን መኾን ግርማዊ አጼ ኃለስላሴ ላደረጉት ጉልህ ሚናም የአፍሪካ አባት የሚል መጠሪያ አስችሯቸዋል።
ለአብነትም ሰንዴይ ኦብዘርቨር የተባለው የናይጄሪያ ጋዜጣ ግርማዊነታቸውን “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት” በሚል ርዕስ የግርማዊነታቸውን ጥረት እና ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከትቦት ይገኛል።
ድርጅቱ ከመነሻው በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ ሀገሮችን ነጻ ማውጣትን ዓላማው አድርጎ ነበር የተመሠረተው። ከኅብረቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በወቅቱ ነጻ ሀገራት 32 ብቻ ነበሩ።
ይህንን መነሻ በማድረግም በቅኝ አገዛዝ የሚማቅቁ የአፍሪካ ሀገሮች ነጻ እንዲወጡ ጥረት አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተለዋዋጩ የዓለም ነባራዊ ኹነት ኅብረቱም ከወቅቱ ጋር ራሱን እንዲያዛምድ ግድ ብሎታል።
በዚህም ከስያሜ ለውጥ ጀምሮ ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ዕደገት ይበጃል የተባሉ አጀንዳዎችን በማስቀመጥ እየተጓዘ 62 ዓመታትን የተሻገረ ድርጅት ኾኗል።
ከአፍሪካ ኒውስ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ጉልህ ሚና መጫወቱ፣ ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መመዝገቡ፣ የአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት የኅብረቱ ዋና ዋና ስኬቶች አድርጎ አስቀምጧል።
ከዕቅድነት የተሻገሩ ባይኾኑም ኅብረቱ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ በሚል በርካታ አጀንዳዎች አሉት። አጀንዳ 2063 የሚባለው ደግሞ በርካታ አፍሪካዊ ጉዳዮችን ያካተተ የኅብረቱ ዕቅድ ዋነኛው ነው። ይህም በ50 ዓመታት ውስጥ አሳካቸዋለሁ ያላቸው ግቦች የተያዙበት ግዙፍ ውጥን ነው።
በአካታች ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ላይ በመመሥረት የበለፀገች አፍሪካን ማየት፣ በፓን አፍሪካኒዝምና በአፍሪካ ህዳሴ ላይ የተመሠረተች የተሳሰረች አህጉርና የፖለቲካ አንድነትን ማምጣት፣ መልካም አሥተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አፍሪካን ማረጋገጥ፣ ሰላማዊ እና ደኅንነቷ የተረጋገጠላት አፍሪካን ማየት፣ ጠንካራ ባሕላዊ ማንነት፣ የጋራ ቅርስ፣ የጋራ እሴት እና ሥነ ምግባር የሚታይባት አፍሪካን መፍጠር፣ ልማቷ በሰዎች ላይ ያተኮረ፣ በአፍሪካውያን አቅም፣ በተለይም በሴቶች እና ወጣቶች ላይ የተመረኮዘ፣ እንዲሁም ልጆች እንክብካቤን የሚያገኙባትን አፍሪካ ማረጋገጥ፣ ብሎም አፍሪካን ጠንካራ፣ የተባበረች፣ አይበገሬ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፋዊ ተዋናይ እና አጋር ማድረግ የሚሉ ዕቅዶችን ያካተተም ነው።
👉የእግር ኳሱ የበላይ ጠባቂ!
በዚህ ሳምንት ከ121 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተወዳጅነት እየጨመረ በመምጣቱ አንድ ወጥ የኾነ የቁጥጥር አካል የማግኘት አስፈላጊነት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በግልጽ ታየ።
በዚህም ምክንያት ፊፋ (Fédération Internationale de Football Association) ግንቦት 21 ቀን 1904 ዓ.ም በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ተመሠረተ።
የፈረንሳይኛ ስሙ እና አህጽሮተ ቃሉም በዓለም ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውልም ይስተዋላል።
የማኅበሩ መሥራች አባላት የቤልጂየም፣ የዴንማርክ፣ የፈረንሳይ፣ የኔዘርላንድስ፣ የስፔን፣ የስዊድን እና የስዊዘርላንድ ብሔራዊ ማኅበራት ነበሩ። በዚሁ ዕለት የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር በቴሌግራም በኩል የመቀላቀል ፍላጎቱን ገልጿል።
የፊፋ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሮበርት ጌሪን ነበሩ። ከዛም በ1906 ዓ.ም በእንግሊዛዊው ዳንኤል በርሊ ውልፎል ተተክተዋል።
ፊፋ ያዘጋጀው የመጀመሪያው ውድድር ማለትም በ1908 ዓ.ም ለንደን ኦሎምፒክ የተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር፣ ከቀደሙት የኦሎምፒክ ውድድሮች የበለጠ ስኬታማ ነበር።
የፊፋ ድረገጽ እንደሚያትተው አባላቱ ከአውሮፓ ባሻገር በ1909 ደቡብ አፍሪካን፣ በ1912 አርጀንቲናን፣ በ1913 ካናዳን እና ቺሊን እንዲሁም በ1914 ዩናይትድ ስቴትስን በመቀላቀል አድማሱን አስፍቷል።
የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ በ1930 ዓ.ም በሞንቴቪዲዮ ኡራጓይ ተካሂዷል።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በርካታ ተጫዋቾች ወደ ጦር ግንባር በመላካቸው እና ዓለም አቀፍ ጉዞዎች በመገደባቸው የድርጅቱ ሕልውና አጠራጣሪ ኾኖም ነበር።
ፊፋ ከነበረበት የኅልውና አደጋ ቢተርፍም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ክልሎች (Home Nations) ከጦርነት ጠላቶቻቸው ጋር በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመኾን በመጥቀስ ከአባልነት ለቀው ነበር።
በኋላ ላይ ግን እንደገና አባልነታቸውን ቀጠሉ። ድርጅቱም እስካኹን ድረስ የሚገጥሙትን ችግሮች እየተሻገረ እስከዛሬዋ ዕለትም የእግርኳሱ የበላይ ጠባቂ ኾኖ ዘልቋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!