
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመምህራን ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ባለፉት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። ከውጤታማ ሥራዎች ጎን ለጎን ደግሞ ፈተናዎች ነበሩ ነው ያሉት። ፈተናዎችን ለመፍታት ደግሞ የምሁራን አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የሚጠየቁ ጥያቄዎችን እና መፈታት የሚገባቸው ችግሮችን ለመፍታት በጋራ የመፍትሔው አካል መኾን እንደሚገባ አንስተዋል። “ሀገር የሚሻገረው በጋራ ችግር ላይ የጋራ መፍትሔ ሲፈለግ ነው” ብለዋል። መፍትሔ ለማምጣት መግባባት እና መተማመን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲ ሀገር የሚያሻግር ሃሳብ የሚመነጭበት ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል። የሕዝብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ሃሳቦችን የሚያወጡ ምሁራን እንዳሉም አንስተዋል።
ችግሮችን በስክነት መመልከት እና በስክነት መመለስ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። መንግሥት ችግሮችን በለውጥ ሂደት ውስጥ እየፈታ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። በችግር ውስጥ ተኹኖ የመጡ ለውጦችን በአውንታዊ ማየት፣ ለገጠሙ ፈተናዎች ደግሞ መፍትሔ መስጠት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ምሁራን ለሀገር ግንባታ እና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል።
የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች ጥያቄዎች ትክክል ናቸው ያሉት ኀላፊው ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ የኾነ ደሞዝ የለም፣ ይሄን ለመቀየር መሥራት አለብን ተብሎ እየተሠራ ነው ብለዋል። ጥያቄዎችን ካልተገቡ ሃሳቦች ጋር ማያያዝ እና ከኾነ ዘመን ጋር እያነጻጸሩ ማንሳት ለዘመኑ እንደማይመጥንም አንስተዋል።
ፍትሐዊ የኾኑ ጥያቄዎችን ለሌሎች አጀንዳ መጠቀሚያ ማድረግ እንደማይገባም አሳስበዋል። ጥያቄዎች የሚፈቱት በውይይት እና በምክክር ነው ብለዋል።
ሁላችንም አንድ ኾነን ክልሉን ማሻገር አለብን ያሉት ኀላፊው ክልሉ ወደ ኋላ እንዳይቀር፣ የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር መተጋገዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሃሳብ ማዋጣት እና የመፍትሔ ሃሳብ ማፈላለግ ከምሁራን እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!