“ለሀገር ችግር መፍትሔ የሚያመነጩት ምሁራን ናቸው” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመምህራን ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ መምህራን የትምህርት ጥራትን በማሻሻል የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ ያላቸው ድርሻ ትልቅ ነው ተብሏል። ይሄን ኀላፊነት እንዲወጡ የመምህራንን ብቃት ማረጋገጥ ይገባል ነው የተባለው።
የትምህርት አሥተዳደርን እና አመራርን ማጎልበት ደግሞ ሌላኛው ጉዳይ መኾኑ ነው የተነሳው። መምህራን ሀገርን ለመገንባት የማይተካ ሚና አላቸው ተብሏል። የተረጋጋች እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት መምህራን ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተነስቷል።

መምህራን እንደ ሀገር ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል። በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲፈጠር በማድረግ፣ ግጭትን በማስቀረት፣ ለመጭው ትውልድ የሰላምን ባሕል የማውረስ ኀላፊነት አለባቸው ነው የተባለው። ትውልድን በሀገራዊ ስሜት እና በመልካም ሥነ ምግባር የመቅረጽ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተገልጿል። ጥቅል ጥናት እና ምርምር በማድረግ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማድረግ ይገባልም ነው የተባለው።

ዜጎችን የሚያቀራርቡ፣ አንድነትን የሚፈጥሩ፣ ሀገርን ወደፊት የሚያሻግሩ ይዘቶች ላይ መሥራት ይገባል ተብሏል። መምህራን መብት እና ግዴታውን በሚገባ እና በሚዛናዊነት የሚጠቀም ዜጋ መፍጠር እንደሚገባቸውም ተነስቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ለጠንካራ መንግሥት ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። ተቋማትን፣ ትውልድን የሚገነባ እና ሀገርን የሚጠብቅ መንግሥት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፣ ይህ የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል፣ ያሳዝናልም ብለዋል።

ነገውን የሚያልም ትውልድ እንዲፈጠር የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባም ተናግረዋል። ከብሽሽቅ ፖለቲካ በመውጣት የፖለቲካ ብልሽትን ማስተካከል እና መግባባት ይጠበቃል ነው ያሉት። መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልማቶችን ማጠናከር እንደሚገባውም ተናግረዋል። ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም ቅደሚያ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞች ለማስከበር የውስጥ አንድነት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል።

የመምህራን ጥያቄ የትውልድ ጥያቄ መኾኑንም ገልጸዋል። መምህራን የሀገር ዋልታዎች ናቸው፣ ትውልድ ይቀርጻሉ፣ ትውልድ ደግሞ ሀገርን ይቀርጻል ነው ያሉት። በመምህራን ላይ ያለው ጫና እና የኑሮ ውድነትን መቋቋም አለመቻል በትውልድ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።

የመምህራን ጥያቄ የቆዬ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ መመለስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። የመምህራን የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸውም ተጠይቋል። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር መምህራን መዋከብ እና እንግልት እንደሚደርስባቸውም አንስተዋል። የጸጥታ ችግር ከማኅበራዊ ሕይዎት እያስወጣቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የመምህራንን ጥያቄ በፖለቲካ ዐይን መመልከት ተገቢ አለመኾኑን እና ፖለቲካዊ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ኀይሎችም መኖር እንደሌለባቸው ገልጸዋል። ፖለቲከኞች እና ምሁራን የሚገናኙበት ድልድይ መሠራት አለበት፣ ኢትዮጵያ ለምን ልጆቿን ታስተምራለች? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ፖለቲከኞች በምሁራን መታገዝ እንደሚገባቸው ያነሱት ተሳታፊዎቹ ምሁራን ፖለቲከኞችን የሚያግዙበትን፣ ላስተማረቻቸው ሀገር አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ተቋም መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ለሀገር ግንባታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በማፍለቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ለሀገር እና ለሕዝብ ይበጃል የሚባልን ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዕውቀት ቋት መኾናቸውንም ተናግረዋል። ለሀገር ችግር መፍትሔ የሚያመነጩት ምሁራን ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ እኛ የመፍትሔ ሃሳብ ካላመነጨን ሌላ ሊያመነጭ አይችልም ነው ያሉት። ፖለቲከኞች ሃሳብ ሲጠየቁ ዕውነተኛ ሃሳብ እና ጥበብን ማጋራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከዚህ እንዴት እንውጣ? የክልሉ መንግሥት ምን ያድርግ? የሚለውን ሃሳብ ማዋጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለመሠረታዊ ጥያቄዎች መሠረታዊ መፍትሔዎችን ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል። በሚቀጥለው ዓመትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ የሚርቁ ከኾነ የትውልድ ከፍተት እውን ሊኾን ነው፤ ለዚህ ደግሞ መፍትሔ መፈለግ አለብን ነው ያሉት።

የመፍትሔ ሃሳቦችን ጥበብ ባለው መንገድ ማቅረብ ለሕዝብ ጥያቄ ሁነኛ መልስ ይዞ ሊመጣ እንደሚችልም አንስተዋል።ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረጉ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። እንደ ምሁር የሚጠበቅን ኀላፊነት መወጣት አስፈላጊ ነው፣ የሚጠቅሙ አስፈላጊ ነገሮችን እያቀረቡ ሀገርን ማገልገል ጠቃሚ ነው ብለዋል።

የሀገር ግንባታው ላይ የምሁራን ሚና ላቅ ያለ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ሀገር እና ሕዝብ ሊለውጥ የሚችል ሀሳብ ለማቅረብ ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ግብረ ገብ ትውልድን በመቅረጽ ሀገራዊ ለውጡን እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ።
Next article“ሀገር የሚሻገረው በጋራ ችግር ላይ የጋራ መፍትሄ ሲፈለግ ነው” አቶ ሲሳይ ዳምጤ