የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ግብረ ገብ ትውልድን በመቅረጽ ሀገራዊ ለውጡን እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ።

17

ደሴ: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ትውልድ በመምህራን ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ውይይት አድርገዋል። በመድረኩ ምሁራን የሀገርን መሠረታዊ ፍላጎት በጥናት እና ምርምር በመለየት ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ እና የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

ሀገርን እና ሕዝብን ከችግር የሚያወጡ፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን ቀድሞ በመለየት ለቀውሱ መፍትሄ መሻት የሚችሉ ብቁ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ማፍራት የመምህራን ቀዳሚ ኀላፊነት መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን ተናግረዋል። እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የገጠሙን የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱት በውይይት መኾኑን የጠቆሙት ምሁራን በሐሳብ ልዕልና የሚያምን ሞጋች እና ምክንያታዊ ደጋፊ ትውልድ የሚፈጠረው በትምህርት በመኾኑ ይህንን ኀላፊነት ለመወጣት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የሥራ አጥ ዜጎች መበራከት የሀገርን አንድነት ለቀውስ ይዳርጋል ያሉት መምህራኑ ሥራ ፈላጊ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን በማፍራት መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ በትኩረት መሥራት ከመምህራን ይጠበቃል ነው ያሉት። በውይይት እና በሕግ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል። ዜጎች በውይይት እና በሐሳብ ልዕልና ካመኑ የሚከሰቱ አለመረጋጋቶች በሂደት ይቀንሳሉ ያሉት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ለሰላም መስፈን ቅድሚያ የሚሰጡ ዜጎችን ማፍራት ተቋማዊ ኀላፊነታቸው መኾኑን ተናግረዋል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ብዥታ የሌለባቸው ንቁ እና ሀገር ወዳድ ዜጎችን ለማፍራት ከታች ጀምሮ መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት። መምህራን ለመማር ማስተማሩ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ጠንቅቀው የሚረዱ፣ ሀገርን የሚለውጡ፣ የሚገጥሟትን ፈተናዎች መቋቋም የሚችሉ እና ከዚያ ፈተና ፈጥና እንድትወጣ የሚጥሩ ብቁ ዜጎችን ማፍራት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

አካባቢያዊ እና ሀገራዊ ችግሮችን በምርምር በመቅረፍ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ የሚሰጥ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባም አንሰተዋል። ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ ከተሠራ ሀገር የምትፈልጋቸውን ዜጎች በየደረጃው ማፍራት እንደሚቻልም ገልጸዋል። የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል (ዶ.ር) በበኩላቸው አዎንታዊ አመለካከት ያለው እና ሰላምን ለማስፈን የሚታትር ትውልድ በመፍጠር በኩል መምህራን ከፍተኛ ሚና አለባቸው ብለዋል።

በተቋም ደረጃ ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህንኑ እቅድ ለማሳካት የትምህርት ሥርዓቱን በማዘመን እና የማሻሻያ ርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑን አንስተዋል። በመምህራን ልማት፣ አሠራርን በቴክኖሎጂ የመደገፍ እና ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የተመሠረተ ምርምር በማድረግ ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ የሚለውጡ ዜጎችን ለማፍራት እንሠራለን ነው ያሉት።

ሀገራዊ ለውጡ በትምህርት ዘርፉ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ውስንነቶችን በማስተካከል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። በዘርፉ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ማምጣቱንም ገልጸዋል። በውይይት እና በሐሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለማፍራት የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ላይ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

ምሁራን የፖለቲካ ምኅዳሩ እንንዲሰፋ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ባለፉት ሰባት ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦችን እና እንደ ሀገር በገጠሙ ችግሮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። በሀገራዊ ጉዳዮች በመነጋገር የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ከገጠሙን ችግሮች መውጫ መንገድ ማመላከት የሚችሉበትን አውድ መፍጠር የውይይቱ ዓላማ መኾኑንም አንስተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ትውልድ በመቅረጽ፣ ግብረ ገብነትን በማስረጽ እና የዴሞክራሲ ምኅዳርን ከማስፋት አንጻር የድርሻቸውን በመወጣት ሀገራዊ ለውጡ እንዲቀጥል እና አካታችነቱ ተጠናክሮ እንዲሄድ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። መምህራን በሀገራቸው አንድነት ላይ የጠራ እና የማይናወጥ አቋም በመያዝ ሀገር ወዳድ ትውልድ የመገንባት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ኪነ ጥበብ የወል ትርክት ለመገንባት እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አይነተኛ መሣሪያ ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ
Next article“ለሀገር ችግር መፍትሔ የሚያመነጩት ምሁራን ናቸው” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)