“ኪነ ጥበብ የወል ትርክት ለመገንባት እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አይነተኛ መሣሪያ ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

32

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሀገር እና ጥበብ፣ ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ በዞኑ ከሚገኙ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ታከለ ሙሉጌታ፣ የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ምትኬ ባዩ እንዲሁም በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ኪነ ጥበብ የወል ትርክት መገንቢያ እና የብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያ አይነተኛ መሣሪያ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ኪነ ጥበብ የአንድን ማኅበረሰብ ወግ፣ እሴት እና ባሕል ከማውጣት እና ከማስረፅ ባለፈ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ዘርፍ መኾኑን ነው ዶክተር አየለ የገለጹት።

ባለፉት ዓመታት ኪነ ጥበብ ያለውን ትልቅ አቅም በበቂ ሁኔታ አልተጠቀምነውም ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በአሁኑ ወቅት መንግሥት ዘርፉን ዋነኛ የትውልድ መገንቢያ መሣሪያ አድርጎ እየሠራበት መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ማኅበረሰቡ ከሚከፋፍል እና ከሚነጣጥል አስተሳሰብ ወጥቶ የሚያሰባስብ፣ አንድ የሚያደርግ እና የጋራ ትርክትን ለመገንባት የሚያስችል አይነተኛ መሣሪያ መኾኑን በውል በመረዳት ለመደገፍም ቁርጠኛ መኾኑን አስታውቀዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ምትኬ ባዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አስተማሪና ገንቢ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ኅብረተሰቡን በማነፅና በማስተማር በኩል ልዩ ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል። የጋራ እሴቶችን በማጎልበት የዜጎችን የሀገር ፍቅር ስሜት በማዳበር፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ መረጋጋት እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።
Next articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ግብረ ገብ ትውልድን በመቅረጽ ሀገራዊ ለውጡን እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ።