መምህራን ሀገር ያለችበትን ችግር በመረዳት ገዥ ሀሳቦችን የማቅረብ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ።

18

ወልድያ: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ትውልድ በመምህር ይቀረፃል፣ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር አካሂደዋል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር መብሬ ታዴ መምህራን የያዙትን ሙያዊ ኀላፊነት ለመወጣት ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለሚሠሩት ሥራም በመንግሥት በኩል ተገቢ የኾነ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

መምህራን ትውልድ ለመቅረጽ አይነተኛ ሚና ያላቸው በመኾኑ ሥራቸው በሚገባ ሊደገፍ ይገባል ሲሉም ለአሚኮ ገልጸዋል። መምህራን ሰላምን ከማስፈን አኳያ ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት መምህር መብሬ ታዴ ሀገር ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በመረዳት ገዥ ሀሳቦችን የማቅረብ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት መምህርት ፈለጉ አታገለ ለማንኛውም የሥራ መስክ ቁልፉ መምህርነት ነው ብለዋል። ሀገር በመገንባት ረገድም ጉልህ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል። መምህር የሚያስተምረው ዕውቀት ብቻ ሳይኾን አመለካከት እና ክህሎትንም ነው፤ ሰላምን የሚሻ በሀሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ የመፍጠር አቅምም አለው ብለዋል።

ይህን አቅሙን በሙሉ እንዲጠቀም ተገቢ ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረጽ ጀምሮ የመምህራንን ጥቅም በማሟላት መንግሥት ጉልህ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው ያስረዱት። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) መምህራን ሚናቸው በየመስኩ ልሂቃንን በማፍራት የሀገርን ልማት እና ዕድገት አስተማማኝ መሠረት ላይ መጣል ነው ብለዋል።

በመኾኑም የትምህርት ተቋማት እና መምህራን ላይ የሚሠራው ሥራ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት መኾኑንም ነው የገለጹት። ዩኒቨርሲቲዎች በሳይንሳዊ እና ማኅበረሰባዊ መስኮች የካበተ ልምድ፣ ዕውቀት እና ክህሎት ያዳበሩ መምህራን መገኛ በመኾናቸው በሀገር ልማት ግንባታ እንዲሁም በሀገር ሰላም እና ዕድገት ላይ ሚናቸው ጉልህ ነው ብለዋል።

እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ እና ጥራት ያለው ትውልድ ከመቅረጽ ጎን ለጎን ሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑንም አስረድተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ትምህርት የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ እድገት መሠረት ነው” አቶ ፍሰሃ ደሳለኝ
Next articleከጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።