“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስተሳሰብ የለማ ትውልድን ለመቅረፅ የጎላ ፋይዳ አላቸው” የደሴ ከተማ አሥተዳደር

15

ደሴ: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና መልካም አሥተዳደር እንዲሁም የመማር ማስተማር ተግባራት ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ ነው። “ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው በዚህ መድረክ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ መምህር ወንድወሰን ይማም መምህራን የንድፈ ሐሳብ እና የተግባር ትምህርትን ከመስጠት በተጨማሪ ትውልድን በመቅረፅ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ ስላላቸው ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የራሳቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ለማድረግ የውይይቱ አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል። ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነፅ ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው መምህር አያሌው ሐሰን (ዶ.ር) ውይይቱ መምህራን በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተደረገውን ለውጥ እና በመጣው ውጤት ላይ የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ በጥናት እና ምርምር በማዳበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል። የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ልክ ለመምህራን ማትጊያዎች ያስፈልጋሉ ያሉት ዶክተር አያሌው መምህራንም የተጣለባቸውን አደራ በውስጣዊ ተነሽነት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ከምሁራን ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል። ውይይቱ መምህራን መንግሥት ለሚሠራቸው ሥራዎችም አጋዥ ስለኾኑ የራሳቸውን አበርክቶ እንዲወጡ ለማስቻል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስተሳሰብ የለማ ትውልድን ለመቅረፅ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ያሉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ውይይት መደረጉ ተቀራራቢ አረዳድ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ገዥ ትርክትን በመገንባት ለሀገር ሰላም እና አንድነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

በመምህራን የሚነሱ ጥያቄዎችም በተቋማዊ አሠራር መሠረት በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉም ከንቲባው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ያለው ግንኙነት ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት ተሸጋግሯል።
Next article“ትምህርት የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ እድገት መሠረት ነው” አቶ ፍሰሃ ደሳለኝ