
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተሻሻለው የዘር አዋጅ 1288/2015ን የማስተዋወቅ እና የሕገ ወጥ ዘር ቁጥጥር ላይ ምክክር እያደረገ ነው። የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ዘላለም ልየው በመድረኩ አጋር አካላት በተሻሻለው የዘር አዋጅ ላይ በመወያየት ሕገ ወጥ የዘር ግብይትን ለመቆጣጠር ተባብረው የሚሠሩበት ዝግጅት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የፍትሕ አካላት ተባብረው በመሥራትም ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር እና ግብይትን በመከላከል ኅብረተሰቡን ከጉዳት የማዳን ኀላፊነት እንዳለባቸውም አንስተዋል። መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የተመሠረተው በግብርና እና አርሶ አደሮች ላይ መኾኑን ጠቅሰው ዘርፉን ለማሳደግ መደገፍ እንዳለበት ገልጸዋል።
አርሶ አደርን በአግባቡ ሳናገለግል ምጣኔ ሀብታችን ማሳደግ አንችልም። ለአርሶ አደሩ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶችም መካከል የተሻሻሉ የዕጽዋት ዘር አንዱ ነው ብለዋል አቶ አጀበ። የክልሉ የዘር አቅርቦት መደበኛ እና መደበኛ ባልኾነ መንገድ እንደሚቀርብ የገለጹት አቶ አጀበ በዘር አቅርቦት ላይ የሚፈጠር መዘናጋት ምርታማነትን እንደሚቀንስ አንስተዋል።
በዘር አምራቾች እና አቅራቢዎች በኩል የሚቀርበው መደበኛ የዘር አቅርቦት በክልሉ ከሚፈለገው 10 በመቶ እንኳ እንደማይሸፍን አንስተዋል። በአርሶ አደሮች ባሕላዊ ሥርዓት የሚቀርበው መደበኛ ያልኾነ የዘር አቅርቦት የሚኖርበትን ውስንነት በማሻሻል ወደ መደበኛ ሥርዓቱ መለወጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አቶ አጀበ በመደበኛ የዘር አቅርቦት የሚመረት ሰብል ምርት ከፍተኛ መኾኑን እና ይህንን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የምክክር መድረኩም አንዱ ዓላማ መደበኛ የዘር አቅርቦት ሥርዓቱ የሚመራበትን ሥርዓት ማሳለጥ መኾኑንም ተናግረዋል። የመደበኛ የዘር አቅርቦቱ በቂ አለመኾን እና የሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እና አቅርቦት የአርሶ አደሩን ሕይወት እንደሚያበላሽ እና ለምርት ዕድገት ማነቆ መኾኑን አንስተዋል።
ችግሩን በመቅረፍ ምርትን ለማሳደግ የልማት እና የሕግ አካላት ተቀናጅተው መሥራት ይገባቸዋል። ስለኾነም ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን እና አቅርቦትን ለመከላከል በአዋጅ ሕጋዊ ድጋፍ ማግኘቱ ጠቃሚ ነው። ይህንን ሕግ ደግሞ ለማስተግበር ተወያይተን ኀላፊነታችን ለመወጣት ሥራ የምንከፋፈልበት ይኾናልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን