
ደሴ: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን እና በወልድያ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ተወካዮች ጋር የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። መሪዎች ወደ ታች በመውረድ እና የኅብረተሰቡን ጥያቄ በማዳመጥ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እየተካሄደ ያለው ጥረት የሚበረታታ መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን በጦርነቱ ምክንያት መጠን ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፓለቲካዊ ኪሳራ አጋጥሞታል ያሉት ተወያዮቹ ዞኑ እንዲያገግም ለማድረግ ሰፊ ሥራ መከናወን አለበት ብለዋል። የሰላምን ዋጋ ትናንት በሰሜኑ ጦርነት ዛሬ ደግሞ በአካባቢያዊ ግጭት አይተነዋል ነው ያሉት። እውነተኛውን ሰላም እንፈልገዋለን ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት ከጦርነት ማትረፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ላይ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባልም ብለዋል። ትምህርት ተቋርጦ፤ ሕዝብ እየታገተ እና እየሞተ፤ እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይዎታቸው እያለፈ ለሕዝብ እቆረቆራለሁ የሚል ቡድን ሊታረም ይገባዋል ነው ያሉት። መንግሥት ዛሬም በሆደ ሰፊነት ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እና በይቅርታ መንፈስ የሰላም ድርድር ማድረግ አለበትም ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የመንግሥት ሠራተኞች ያነሱት ሃሳብ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል። ሕዝቡ ጥቃት እየተፈጸመበት ያለው በራሱ ሰዎች መኾኑ ያሳዝናል ነው ያሉት። ጽንፈኛው ቡድን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ብሎ የሚያነሳው ለሽፋን እንጅ ዋና ዓላማው ሥርዓት አልበኝነት መኾኑ ግልጽ እየኾነ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ሰላምን ሁሉም ሊንከባከበው የሚገባ መሠረታዊ ነገር ነው ያሉት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ናቸው። የሰላም መደፍረሱ ምክንያት በአማራ ሕዝብ ጥያቄ እየነገደ ባለው ጽንፈኛ ቡድን መኾኑን ልንረዳው ይገባል ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄን አማራን በማፈን፣ ትምህርት በማዘጋት እና መሰል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ሊፈታ አይችልም ነው ያሉት።
የዞኑን ሰላም ማስፈንም ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይኾን ሁሉም አካል ሊሳተፍበት የሚገባ ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ የመንግሥት ሠራተኞች የመንግሥትን ዕቅድ፣ ሰላም እና የኢኮኖሚ ግስጋሴን ለማሳካት ወሳኝ መኾናቸውን አንስተዋል።
ጽንፈኛው ቡድን የፖለቲካ ነጋዴ እና የአማራ ሕዝብ ጥያቄን የዳቦ ስም በመስጠት እያሳሳተ ያለ ኃይል መኾኑ በተግባር ታይቷል ነው ያሉት። የመንግሥት ሠራተኞች በዚህ ቡድን የውሸት ፕሮፖጋንዳ መታለል የለባቸውም ብለዋል። መንግሥት ለሰላም ዝቅ ብሎ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ፍስሀ ዛሬም ለሰላም በሮች ክፍት መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የሕዝብ ችግር የሚፈታው ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖር መኾኑን መገንዘብ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን