“የዳኝነት ነጻነት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችል የማዕዘን ድንጋይ ነው” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

13

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለአማራ ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ዳኞች፣ ለክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እንድሁም ለተለያዩ የፍትሕ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
ሥልጠናው የዳኝነት ነጻነት በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ያለው አንደምታ እና የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ ነው።

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ተገኝተዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት የሥልጠናው ዋና ዓላማ የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኛነት ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ያለውን ፋይዳ ለማስጨበጥ ነው ብለዋል።

እንደ አማራ ክልል ለተገልጋዮች ፈጣን እና ወጭ ቆጣቢ የፍትሕ እና የዳኝነት አገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት በርካታ የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። የተሳለጠ የፍትሕ ሥርዓትን ለማስፈን ደግሞ ጠንካራ እና የተቀናጀ ተቋም ያስፈልጋል ነው ያሉት። ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቢ ሕግ፣ መርማሪ ፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ኦፊሰሮች ጭምር የየራሳቸው የኾነ ነጻነት እና ገለልተኛነት ኖሯቸው መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። የሙያ ነጻነት ባደገ ቁጥር ለዜጎች የተሻለ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም ብለዋል።

ሰብዓዊ መብትን የማክበር እና የማስከበር ጉዳይ ለኾነ አካል ብቻ በኀላፊነት የሚሰጥ አይደለም፤ ሕግ አውጭው፣ አሥፈጻሚው እና ሕግ ተርጓሚው ሁሉ በጋራ በመቆም የዜጎችን መብቶች የማስከበር ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት። ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል እንጅ ብቸኛው የመብቶች አስከባሪ ተቋም አይደለም ሲሉም ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፍርድ ቤቶች የዜጎች የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ ተቋማት መኾናቸውን በመገንዘብም ለማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል። የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ እየተተገበረ እንደሚገኝም አንስተዋል። ለረጅም ጊዜ ጥያቄ እያስነሳ የነበረው የዳኞች ያለመከሰስ መብትም በአዋጅ ጸድቆ ምላሽ አግኝቷል ብለዋል።

የዳኞች ያለመከሰስ መብት ለግለሰብ ዳኞች ጥቅም ሳይኾን ለሕዝብ ጥቅም የቆመ ስለመኾኑም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ዳኞች ከጫና ነጻ ኾነው እና በመረጃ እና በማስረጃ ብቻ ተመሥርተው ሢሠሩ ለተገልጋዩ ሕዝብ እርካታን እንደሚያረጋግጡም አብራርተዋል። ዳኞች በጫና እና ፍርሃት ውስጥ ኾነው በሚሰጡት ፍርድ ትክክለኛ አገልግሎትን ለማግኘት ያስቸግራል ሲሉም ገልጸዋል።

በሥልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የዳኝነት ነጻነት ከራሱ ከዳኛው እና ከሚሠራበት ተቋም ይመነጫል ብለዋል። ዳኛው በራሱ ከየትኛውም ወገን ነጻ ኾኖ መቆም፣ ተቋማትም ለዳኞች ነጻነትን መስጠት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

“የዳኝነት ነጻነት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የማዕዘን ድንጋይ ነው” ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ ጥፋት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲኾኑ እና ተጎጅዎች ተገቢውን ማካካሻ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሰላም ጊዜም ይሁን በግጭት አውድ ውስጥ የሰዎች መብቶች እንዳይጣሱ ክትትል ያደርጋል ብለዋል። የክትትሉ የመጀመሪያ ዓላማ የመብት ጥሰቶችን ቀድሞ ለመቆጣጠር ሲኾን ተጥሰው ሲገኙም ተከታትሎ ለማረም፣ በጥፋተኞች ላይም ተጠያቂነትን ለማስፈን መኾኑን አብራርተዋል።

የዛሬው ሥልጠና ዋና ዓላማም ጠንካራ የኾነ የዳኝነት ነጻነት እና ገለልተኛነትን ለማስፈን ነው ብለዋል። ዳኞች ኅላፊነታቸውን በሚወጡበት ጊዜ የሚደርስባቸውን እንግልት ለመቅረፍ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ቀደም ሲልም ውይይቶች ተደርገዋል፣ ችግሩን ለመቅረፍም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዋጅ አውጥቶ እየሠራበት እንደኾነ ተናግረዋል።

አዋጅ መውጣቱ ብቻ ለውጥ አይኖረውም፤ አዋጁን ወደ ተግባር መተርጎም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በሀገራችን ትላልቅ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽመውም ተጠያቂነትን በማስፈን እና ተጎጅዎችን በመካስ ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አስታውሰዋል።

ይህም ሀገራችንን ለትላልቅ ግጭቶች ዳርጓል ነው ያሉት። እነዚህ ትላልቅ የመብት ጥሰቶች እንዲታረሙ፣ ተጎጅዎች እንዲካሱ እና የመብት ጥሰቶች ዳግም እንዳይከሰቱ በማሰብ የሽግግር ፍትሕ እንደ ፖሊሲ መቀረጹንም ተናግረዋል።

በሥልጠናው እንደ ሀገር የተያዘው የሽግግር ፍትሕ ምን ዓይነት አተገባበር ሊኖረው እንደሚገባም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። የሽግግር ፍትሕ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ባከበረ እና ተጎጅዎችን ባማከለ መልኩ ተፈጻሚ እንዲኾን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ክትትል እንደሚያደርግም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢ-ኮሜርስ የንግድ ዘርፍን ለማሳደግ እንደሚሠራ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleሕዝቦች ጥቃት እየተፈጸመባቸው ያሉት በራሳቸው ሰዎች መኾኑ ያሳዝናል።