
አዲስ አበባ: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር እና በየብስ ላይ ያሉ የሎጀስቲክ ሥራዎችን በማዘመን እና ፈጣን በማድረግ የኢ-ኮሜርስ የንግድ ዘርፍን ለማሳደግ እንደሚሠራ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል። የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር የኢ-ኮሜርስ ሎጀስቲክ ዘርፍን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በኅብረት እየሠራ መኾኑ ተገልጿል።
ኅብረቱን ለማሳደግም ከመንግሥት እና ከግል ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለኢ-ኮሜርስ ሎጀስቲክ ተግዳሮት እና መፍትሔዎች ላይ ውይይት አካሂዷል። ለሀገር ዕድገት ሎጅስቲክ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቀሱት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ድኤታ ዴንዴ ቦሩ የታሰበውን የሀገር ብልጽግና ከፍ ለማድረግ የኢ-ኮሜርስ የንግድ አሠራር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የኢ-ኮሜርስ ሥራውን ይበልጥ ፈጣን እና የተቀናጀ ለማድረግ ሕጎችን እና የሎጅስቲክ አካሄዱን ለማስተካከል ሥራዎች እንደሚሠሩ ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል። ኢ-ኮሜርስ በትልቅ ፍጥነት እያደገ እንዲመጣ መንግሥት ያሉ የሕግ ክፍተቶችን በማስተካል ኢ-ኮሜርስ የሥራ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ጋር ሰፊ ኅብረት ሊያደርግ እንደሚገባም የንግዱ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን