
ደሴ: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2015/2016 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶች ላይ በተሰጠው የኦዲት አስተያየት መሠረት የእርምት ርምጃ ወስደው ያላስተካከሉ ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ አካሂዷል፡፡
ለኦዲት ግኝቶች ምላሽ አለመስጠት፣ ገቢ የተሠበሠበበት ደረሰኝ አለማቅረብ፣ የነዳጅ እና የበጀት አጠቃቀም ክፍተት የሚሉት በተቋማቱ የኦዲት ግኝቶች ላይ የታዩ ክፍተቶች መኾናቸው በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡ ከአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱ አስተያየቶችን በመቀበል የነበረባቸውን ክፍተቶች ለማስተካከል በትኩረት እንደሚሠሩ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ መላኩ ሚካኤል እና የደሴ ዙሪያ ወረዳ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙባረክ ሽፈራው ተናግረዋል።
የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ ተበጀ የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ከዚህ ቀደም የከፋ ኦዲት ግኝት የነበረበት ተቋም እንደነበር አንስተዋል። የተሻለ አሠራር በመዘርጋት እና የኦዲት ግኝታቸውን በማሻሻል ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ የሚኾን ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እመቤት ከበደ ተቋማት የመንግሥትን እና የሕዝብን ሀብት በሚገባ እንዲጠቀሙ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የሚያቀርበውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ መድረኮችን የማዘጋጀት እና ተገቢውን ክትትል የማድረግ ሥራን እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ፊኒክስ ሀየሎም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን