
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን የጠበቁ እልፍ ጉዳይ አትርፈዋል፤ ትውልድን ጠብቀዋል፤ ልማትን አረጋግጠዋል፤ ሞት እና ውድመትን አስቀርተዋል። ሰላም በጠፋ ጊዜ ሰዎች ይሞታሉ፤ ንብረት ይወድማል፤ ልማት እና እድገት ይቀጭጫል። ግጭት ዘመንን ይበላል። ተስፋን ይወስዳል፤ ሕልምን ያጨናግፋል።
በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ አስቀርቷቸዋል። ብዙዎች ነግደው እንዳያተርፉ አድርጓቸው ቆይቷል። እልፎች ከወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይገናኙ፣ በዘሀን እና በደስታው እንዳይደራረሱ አድርጓቸው ከራርሟል። እኒያ ጎብኝዎች የሚመላለሱባቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች ሰው እስኪናፍቃቸው ደረስ ተጎድተው ቆይተዋል። ንጹሐን ተወልደው ባደጉበት ሀገር እየታፈኑ ገንዘብ ተጠይቆባቸዋል። መክፈል ያልቻሉት ተንገላተዋል። ይህን ሁሉ ያመጣው ግጭት እና ልዩነትን በውይይት ያለ መፍታት አባዜ ነው።
በክልሉ አሁን ላይ የተሻለ እና ።ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሄደ ሰላም ተፈጥሯል። ይሄን ሰላም የበለጠ ለማስፋት እና ዘላቂ ለማድረግ ደግሞ እየተሠራ ነው። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን እና እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሉን እያጠናከሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሉን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት። አሁን ያለው የጸጥታ ኃይል የመፈጸም ብቃቱ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል። አሁን ላይ ያለው የክልሉ ግጭት የሽፍትነት ባህሪ ነው፤ መዋጋት የሚችል ጽንፈኛ የለም፤ ጽንፈኛ ኃይሉ በሚወራለት ልክ አይደለም ነው ያሉት። ችግርን በውይይት መፍታት ለልማት ዕድል መሥጠት ነው ያሉት ኀላፊው ነገር መቆስቆስ ሕዝብን ማቆርቆዝ እና ማደህየት ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅት ለማደግ እና ደህነትን ለማሸነፍ ሌት ከቀን መሥራት እንጂ በሰላም ወጥቶ ስለ መግባት መጨነቅ አይገባም፤ ይህ ለዚህ ዘመን አይመጥንም ነው ያሉት። ለሀገር የሚቆረቆር፤ ለሕዝብ የሚታገል ሰው ትውልድ እንዲማር መፍቀድ እንጂ መከልከል የለበትም ነው የሚሉት። ሕዝብን ለጥቅም አሳልፎ መስጠት፤ ተማሪዎች ሁለት ዓመታት ከትምህርት እንዲርቁ ማድረግ ጤነኝነት አለመኾኑንም አንስተዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት ያንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ያሉት ኀላፊው የሰላም አማራጭ ተዘግቶ አያውቅም፤ ሁልጊዜም ክፍት ነው፤ የሰላም አማራጮችን የተጠቀሙትን ተንከባክበን አሠልጥነን ወደ ሰላማዊ ሕይዎት እየመለስን ነው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ሀገርን የሚያሻግረው ሰላም ነው ያሉት ኀላፊው የታጠቁ ኃይሎች ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ዕድሉን መጠቀም አለባቸው ብለዋል። በኃይል ማሸነፍ እንደማይቻል ማወቅ አለበት፤ ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም አለበት ብለዋል። በመጨረሻም ሰላምን መምረጡ ለማይቀረው ጊዜ መውሰድ አይጠበቅም ነው ያሉት።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በየአካባቢው ያለውን የታጠቀ ኃይል እየመከሩ ማምጣት እንደሚገባቸውም አንስተዋል። የሰላም አማራጭን የማይጠቀም ኃይል ላይ የሕግ ማስከበር ሥራችን ይቀጥላል ነው ያሉት። የሰላም አማራጭን ነገ ሳይኾን ዛሬ መጠቀም ይገባል፣ የሚያልፈው የልማት እና የእድገት ጊዜ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ በቃ በነጻነት ተንቀሳቅሸ ማልማት አለብኝ ማለት ይኖርበታል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ተጎድቷል ያሉት ኀላፊው የንግዱ ማኅበረሰብ ነግዶ እንዲያተርፍ፤ ሰላምን መጠቀም እንደሚገባውም ገልጸዋል። የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ፤ ልማት እንዲሰፋ፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ሰላም ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። የተማረ ሰው ችግር ሲገጥም መፍትሔ ማምጣት አለበት ያሉት ኀላፊው ሀገር ሰላም እንዲኾን ለችግሮች መፍትሔ ማበጀት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል። ምሁራን የመፍትሔ ሃሳብ በማፈላለግ ግንባር ቀደም ሚና መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ሕዝብን እንደማይጠቅም ገልጸዋል። ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ተጠቃሚ ለመኾን ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል ነው ያሉት። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ግጭት የሚቀሰቅሱ የሚዲያ ሰዎችም ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብለዋል። በትውልድ ላይ ጠባሳ የሚጥሉ፤ ጠብን የሚጭሩ፣ ልዩነትን የሚሰብኩ አካላት መታረም እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ሚዲያዎች ሰላምን መገንባት እና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የሚዲያ አካላት የሰላም ግንባታ ሚናቸው ላቅ ያለ መኾኑንም ተናግረዋል። ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ ማበረከት እንደሚገባውም አሳስበዋል። “ሰላማዊ አስተሳሰብ መጎልበት አለበት” ያሉት ኀላፊው ሰዎች ስለ ሰላም ያላቸው እይታ መቀየር እንደሚገባውም አንስተዋል። ከሁሉም ነገር በፊት ሰላም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። በየአካባቢው ሰላምን የሚያውክ እንቅስቃሴን መከላከል፣ ሌባን እና ዘራፊን መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ የታጠቁ ኀይሎችን ሰላማዊ አማራጮችን ተጠቀሙ፤ ካለበለዚያ አጋልጬ እሰጣችኋለሁ ማለት እንዳለበትም አንስተዋል። በመተጋገዝ እና በመረዳዳት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን