
ጎንደር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በንግዱ እና ገቢ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል። የሕገ ወጥ ንግድ መበራከት፣ አገልግሎት አሰጣጡን አለማዘመን፣ ሕገ ወጥ ደላሎች መበራከት እና ገቢን ያላገናዘበ ግብር መጣል ለንግድ ሥራቸው እንቅፋት እንደፈጠረባቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ፀጋዬ እንዳሉት ተቋማቸው እየሠራው ባለው ተግባር የንግድ ፈቃድ አሰጣጡን ማዘመን ተችሏል። ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የጎዳና ላይ ግብይትን ማስቀረት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በከተማው ትልልቅ ጅምላ ነጋዴዎችን መፍጠር አለመቻል የንግድ ሥርዓቱን እንደጎዳው ያነሱት ኀላፊው ለመፍትሔው እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። ከልክ በላይ ክፍያ በሚጠይቁ ጫኝ እና አውራጆች ላይ የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወሰድም አመላክተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጥሩየ አትክልት ግብር ለሀገር ልማት ግንባታ የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል። በነጋዴዎች ገቢን ያላገናዘበ ግብር ይጣላል የሚለውን ቅሬታ ለመፍታት ሕግን የተከተለ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ለነጋዴ እና ለነዋሪዎች ምቹ የኾነች ከተማን ለመፍጠር እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል። የገቢ ተቋሙን አሠራር የማዘመን ተግባር እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።
የከተማዋ ዕድገት እንዲፋጠን ነጋዴዎች የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉ ያሳሰቡት ደግሞ በምክትል ከንቲባ መዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም ናቸው።
የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ቦታ በማስረከቡ ረገድ ጥሩ ጅምር መኖሩንም አስረድተዋል።
የውጭ ምንዛሬ መጨመር፣ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት የንግዱን ዘርፍ እንደፈተነውም በውይይቱ ተነስቷል።
ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን