
ፍኖተ ሰላም: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ከወረዳዎች ከተውጣጡ ነጋዴዎች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ነጋዴዎች የጸጥታ ችግሩ ከጀመረ አንስቶ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት በርካታ ችግሮች እየገጠሟቸው መኾናቸውን ተናግረዋል።
እንደልብ ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ሰላም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የሰላሙ ሁኔታ እንዲረጋጋ የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብንም ብለዋል።
መንግሥትም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ እያጋጠሙ ያሉ የመልካም አሥተዳደር እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን እንዲፈታ ጠይቀዋል። በኅብረተሰቡ ላይ እየደረሱ ያሉ ቀውሶችን በዘላቂነት ለመፍታት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም አንስተዋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ የንግዱ ማኅበረሰብ ያለውን ግጭት ከሚያባብሱ ድርጊቶች ራሱን በማራቅ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መሥራት ይገባዋል ብለዋል።
መንግሥትም ከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አማካሪ ይትባረክ አወቀ ከመሠረተ ልማት ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የሰላም ግንባታውን ከመሥራት ጎን ለጎን የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን