ሕዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት ያሳየውን የመተባበርና የመደጋገፍ መንፈስ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደሩ አሳሰቡ።

183

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የዘንድሮ የረመዳን ወር ያለፈው የኮሮናቫይረስ በዓለምና በኢትዮጵያ ላይ ስጋትም ጥፋትም እያደረሰ ባለበት ወቅት መሆኑን ርእሰ መሥተዳድሩ አስታውሰዋል።

የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በዚህ ቅዱስ ወር በታላቅ መሰብሰብና ስግደት ያከብሩት የነበረ እንደሆነ አስታውሰው ዘንድሮ በዚህ መልኩ ለማበር ሁኔታው አለመፍቀዱን አመላክተዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ለሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች በሚያስተምር መንገድ ጾምና ስግደቱን በቤቱ ሆኖ በማሳለፍ የሚያስመሰግን የመከላከል ተግባር እየተወጣ መቆየቱን ያስታወቁት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥንቃቄው በበዓሉ ዕለትም ሆነከዚያ በኋላ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮቹ ሌሎችን ለመርዳት ሲያደርጉት የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር መመልከታቸውንም ገልጸዋል፤ ምሥጋናም አቅርበዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭት በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብርና ለበዓሉ የሚሆን ግብዓቶችን ሲገዛ አስፈላጊውን አካዊ ርቀት እንዲጠብቅና ጥንቃቄ አድርጎ እንዲከውንም አሳስበዋል።

መላው ሕዝበ ሙስሊምና ሌላውም ሕዝብ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርጋቸውን ጥረቶች መደገፍና መፈጸም እንዳለባቸውም አቶ ተመሥገን አስገንዝበዋል፡፡

ቫይረሱ በየጊዜው እየጨመረ አሳሳቢነቱ በመባባሱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ይህንን መጥፎ ጊዜ ማለፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት ያሳየውን የመተባበርና የመደጋገፍ መንፈስ ሙሉ በሙሉ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ከቫይረሱ ስጋት ነፃ መሆን እስኪቻል ድረስ ጥንቃቄ እንዳይለይም ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ አሳስዋል።

ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በባሕር ዳር በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የዕለት ጉርስ ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleHirkoo, Caamsaa 15/2012