ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት የዩንቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ።

13

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ከደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ከመማር ማስተማሩ ተግባር ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉበት አቅም እንዳለ አቶ በድሉ ገልጸዋል፡፡

በተቋሙ ውስጥ ያለው ብዝኀነት የማስተናገድ፣ በልዩነቶች ውስጥ ያለ አንድነትን የማሳየት ልምድ ሁሉም ጋር ተዳርሶ በሰላም እሴቶች ግንባታ ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው በጎ አሻራዎችን ማስቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ አማካሪ ባዬ አለባቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሰላም እጦት መንስኤ የኾኑ ችግሮችን መለየት፣ መተንተን እና መፍትሄ በማመላከት ሂደት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሚሠራቸው የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ይሄንን ግዙፍ ሀገራዊ ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየገቢ ግብርን በትክክል እና በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኀላፊነትን መወጣት ይገባል።
Next articleፋይዳ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመሥጠት እና ፍትሐዊ አሠራርን ለመዘርጋት እንደሚያግዝ የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ አስታወቀ።