የገቢ ግብርን በትክክል እና በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኀላፊነትን መወጣት ይገባል።

15

ደብረብርሃን: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ከዞኑ ከተውጣጡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት እያደረገ ነው። የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዘውገ ንጉሴ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ያሉ እንከኖችን ለይቶ መፍትሔ በመስጠት ሂደት በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ትልቅ ኀላፊነት ወድቋል ብለዋል፡፡

የንግድ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት በምርት አምራች እና አቅርቦት ዘርፉ ላይ ስምሪት የወሰዱ የንግዱ ማኅበረሰብ ሚናን በአግባቡ ለይቶ መወጣት የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሰዓዳ ኢብራሂም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሠራ ባለው ሥራ አዳጊ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሂደት የንግዱ ማኅበረሰብ ድርሻ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በጸጥታው ችግር ምክንያት በማይመች ሁኔታም ውስጥ ተኾኖ መደበኛው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ሲሠራ መቆየቱ አንዱ የጥንካሬ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ የንግድ ሥራን ማከናወን፣ ዘርፉን ለመምራት ለተቀመጡ ሕጎች ራስን ተገዥ አድርጎ መንቀሳቀስ እና የገቢ ግብርን በትክክል እና በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኀላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አብርሃም አያሌው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ውስጥ የንግዱ ዘርፍ አበርክቶ ግልጽ እና ብርቱ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ነው ብለዋል፡፡ ኾኖም የሰላም እጦቱ ይሄንን ወሳኝ ዘርፍ በፈተና ውስጥ እንዲያልፍ እና ውጤታማነቱንም ሲያስተጓጉል መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ በሚያከናውናቸው ተግባራት በውስጥ አቅም ራስን ለመቻል እና ሀገራዊ ድምር ዕድገት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ጤነኛ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት፣ ልዩ ኾኖ መሥራት፣ የገበያ አማራጮችን ማስፋት፣ አብሮ ማደግን መልመድ እና በታማኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleኢትዮጵያ ከዚህ በፊት እንደነበረው የቀይ ባሕር እና የባሕረሰላጤው አካባቢ ተመልካች አትኾንም።
Next articleሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት የዩንቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ።