“ከሰላም ውጭ ሌሎች አማራጮች አያዋጡም” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ላይ ነው። ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችም በርክተዋል። ውይይቶችም ፍሬ እያፈሩ ነው። በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የሰላም አማራጮችን የሚመርጡትም እየበዙ ነው። ይህ ደግሞ በክልሉ ያለውን ሰላም የበለጠ ዘላቂ እና አስተማማኝ እንዲኾን እያደረገው ይሄዳል።

ስለ ሰላም የሚዘምሩት፣ ስለ ሰላም የሚሰብኩት፣ ስለ ሰላም የሚወያዩት እና ሰላምን ለማጽናት የሚተጉትም በርክተዋል። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም የአማራ ክልል ባለፉት ጊዜያት በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል። ችግሩ ክፉ ጠባሳ የጣለ ክስተት ነበር፣ በሰው ሕይዎት፣ በንብረት እና በሥነ ልቦና ላይም ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ግን በክልሉ የተረጋጋ ሰላም አለ፤ በየአካባቢው ያሉ የአሥተዳደር እርከኖች መንግሥታዊ አመራር የሚሰጥባቸው ናቸው ብለዋል። የጸጥታ መዋቅሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማድረግ አቅሙ እያደገ፣ የመፈጸም አቅሙ ከፍ እያለ መሄዱንም አንስተዋል። ሕዝብን ባለቤት በማድረግ የሰላም ሁኔታውን የበለጠ የተሻለ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ወርደው ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ ነው ያሉት ኀላፊው አውዳሚ ሃሳቦች እንዲታረሙ፣ ጽንፈኛ ኃይሉ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ፣ ለሰላም እና ለውይይት ራሱን እንዲያዘጋጅ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

የጸጥታ ኃይሉ አካባቢዎችን በተገቢው መንገድ እየመራ እና ሰላምን እያረጋገጠ መኾኑንም አስታውቀዋል። ለአማራ ክልል ሕዝብ የሚበጀው ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው ያሉት ኀላፊው ግጭት አውዳሚ ነው፣ የኋላቀርነት አስተሳሰብ መገለጫ ነው ብለዋል። በየአካባቢው የሚደረጉ ውይይቶች ሕዝቡ በቃ እንዲል እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መረጋገጥ እየሠሩ ነው ያሉት ኀላፊው በግጭት ውስጥ ያሉትን እየያዙ እያመጡ ሰላማዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በግጭት ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎችም ግጭት ስህተት መኾኑን እያመኑ፣ የአማራ ክልልን ሕዝብ አጎሳቁያለሁ እያሉ፤ በድያለሁ እያሉ የሰላም አማራጮችን እየተቀበሉ ነው፤ ይህን ያመጣው ደግሞ ውይይት ነው፤ ውይይቶቹ ብዙ ነገር ቀይረዋል፤ ውጤትም አምጥተዋል ነው ያሉት። የጽንፈኛው አቅም እየደከመ መሄዱንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እንዳላገኝ አደረጋችሁኝ፣ ልጆቼ እንዳይማሩ ከለከላችሁብኝ፣ የግብርና ግብዓት እንደ ፈለግን እንዳይመጣ አደረጋችሁብኝ እያለ ከጽንፈኛው ላይ ፊቱን እያዞረበት ነው ብለዋል።

በየጊዜው የሰላም አማራጮችን የሚጠቀሙ ኃይሎች አሉ ያሉት ኀላፊው መንግሥት የሰላም አማራጮችን የሚጠቀሙትን እየተቀበለ፣ እያሠለጠነ፣ የሚቋቋሙበት ገንዘብ እየደገፈ ወደ ማኅበረሰቡ እየቀላቀለ መኾኑን ነው ያነሱት። መንግሥት በሆደ ሰፊነት ብዙ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። “ከሰላም ውጭ ሌሎች አማራጮች አያዋጡም” ያሉት ኀላፊው መንግሥትን በኃይል ማፍረስ አይቻልም፤ ፈተና እና ትግል ያጠበቀው መንግሥት ነው፤ ሠራዊቱ በፈተና ውስጥ ተፈትኖ ድል ያደረገ ነው፤ በግጭት የሚሳካ የለም፤ የሚያዋጣው ሰላማዊ አማራጭ ነው ብለዋል።

ታጣቂ ኃይሎች ከስህተት መማር፣ ግጭት እንደማያዋጣ ማመን ይገባል፤ የእርቅ፣ የሰላም፣ የውይይት አማራጮችን መምረጥ ይጠበቃል ነው ያሉት። ብዙ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አናብርም፣ አካሄዳችን ልክ አልነበረም እያሉ እየገቡ ነው፤ የእነዚህ አካሄድ የሚመሰገን እና የብልህነት አካሄድ ነው ብለዋል።

የአማራን ሕዝብ እና መንግሥት በጠላትነት ከሚያይ ኃይል ጋር አናብርም እያሉ ብዙዎች እየመጡ ነው፤ ሌሎችም ይሄን አካሄድ መከተል አለባቸው ነው ያሉት። ልጆች እንዳይማሩ መፍረድ ምን ማለት ነው? የሚሉት ኀላፊው ግጭት ትውልድን ከመግደል የዘለለ ጥቅም የለውም፤ የሰላም አማራጮችን እስካሁን ያልተቀበሉትም ቆም ብለው አስበው ሰላምን መምረጥ አለባቸው፤ ምክራችን ይህ ነው ብለዋል።

መንግሥት አሁንም የሰላም አማራጩ ክፍት ነው፣ በየአካባቢው ካሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር እየተነጋገሩ ሰላምን መምረጥ ይገባቸዋል ነው የሚሉት። የእኛ ጀግና እያሉ ሀገር እንዲወድም የሚገፋፉ አይጠቅሟቸውም፣ የሚጠቅማቸው ሰላም እና ሰላም ብቻ ነው ይላሉ።

ኅብረተሰቡም ልጆቹን መምክር፣ ወደ ሰላም መመለስ አለበት፤ ከአውዳሚ ጋር መተባበር አያስፈልግም ነው ያሉት። ሁለት ዓመታት ትምህርት ማቋረጥ በቀላል የሚታይ አይደለም፣ ይሄን የሚያቋርጥ ኀይልን ማውገዝ ግድ ይላል፣ አባቶቻችን ሕዝብን እና ሀገርን ከጠላት ነው የተከላከሉት ነው ያሉት። አሁን ያሉት ጽንፈኞች ግን የራሳቸውን ሕዝብ ነው ለችግር የዳረጉት፣ ይሄን አካሄድ ማውገዝ እና በቃ ማለት የተገባ ነው ይላሉ።

ለሕዝብ የሚያስብ ሕዝብን አይዘርፍም፣ ትምህርትን አይዘጋም፣ ንጹሐንን አያግትም፣ ይህ ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፣ ሕዝብን ወደ ቁልቁለት ጉዞ የሚገፋ ነው፣ ሰክኖ ማሰብ፣ አርቆ ማየት፣ ሰላምን ማስቀደም እና ለሕዝብ መቆም ይገባል ነው ያሉት። ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ኑሮየ በመስኖ ስንዴ ልማት ተለውጧል” አርሶ አደር
Next articleኢትዮጵያ ከዚህ በፊት እንደነበረው የቀይ ባሕር እና የባሕረሰላጤው አካባቢ ተመልካች አትኾንም።