
ባሕር ዳር፣ ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ለጋንቦ ወረዳ ደረባ 020 ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ስዩም አዛዥ፣ የመስኖ ልማት ሥራን ለረጅም ዓመታት በዘልማድ ሲጠቀሙ እንደነበር ይናገራሉ። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ግን በባለሙያዎች ድጋፍ ዘመናዊ አሠራር እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንዲኹም በክላስተር በመዝራት የተሻለ ምርት ማግኘት ችለዋል።
“ከዚህ በፊት በግማሽ ሄክታር ከስድስት እስከ ሰባት ኩንታል አገኝ ከነበረው፣ አኹን 17 ኩንታል እና ከዚያ በላይ ምርት ማግኘት ችያለሁ” ያሉት አርሶ አደር ስዩም ይህ ለውጥ ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ኑሮአቸውን ወደ ኪሳቸው ገንዘብ ወደሚያስገቡበት ደረጃ እንዳሸጋገራቸው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ ቤት ለመሥራት እና የእህል ወፍጮ ለመትከል መብቃታቸውንም ተናግረዋል።
የለጋንቦ ወረዳ በ2017 በጀት ዓመት 1ሺህ 547 ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አቅዶ 1ሺህ 596 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት በማልማት ከዕቅዱ በላይ ማሳካት ችሏል። የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሁሴን ሙላት እንዳሉት ይህ የተገኘው አዳዲስ የግብርና አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ከዕቅድ በላይ ለማምረት በተደረገ ርብርብ ነው።
በዚህ ሥራ ላይ 10ሺህ 920 ሰዎች ተሳትፈዋል። ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም 2ሺህ 461 ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እና 2ሺህ 394 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል። ለአርሶ አደሩ እና ለግብርና ባለሙያዎች የቅድመ ዝግጅት ሥልጠና መሰጠቱንም አቶ ሁሴን ገልጸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የቢጫ ዋግ በሽታም መድኃኒቶችን በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሉን ተናግረዋል።
አኹን ባለው የሰብሉ ቁመና ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ እና የሰብል ባለሙያ ተስፋዬ መርቆሪዮስ በበጀት ዓመቱ ከአጠቃላይ በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 21ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
20ሺህ 138 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር መሸፈን እንደተቻለ የገለጹት ባለሙያው ይህም የዕቅዱን 94 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል። ይህንን ምርት ውጤታማ ለማድረግ በሁሉም ወረዳዎች የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት አርሶ አደሩ ለሥራው ፍላጎት እንዲኖረው መሠራቱን ተናግረዋል።
በሰብል ከተሸፈነው ውስጥ እስካኹን ባለው ወደ 6ሺህ 965 ሄክታር መሬት ላይ ምርት መሠብሠብ የተቻለ ሲኾን በዚህም ወደ 272ሺህ 21 ኩንታል ምርት መገኘቱን ባለሙያው ገልጸዋል። በቀሪዎቹ ወራቶች የሰብሉ ቁመና ጥሩ በመኾኑ እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን