
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፒ.ኬ.አይ (ፐብሊክ ኪ ኢንፍራስትራክቸር) በበይነ መረብ አማካይነት የሚደረግ ማንኛውም የመረጃ ልውውጥ እና ግብይት ምሥጠራን (ኢንክሪፕሽን) እና ዲጂታል ማረጋገጫን (ዲጅታል ሰርቲፊኬት) በመጠቀም ልውውጡ ደኅንነቱ የተጠበቀ መኾኑን የሚረጋገጥበት መሠረተ ልማት ነው፡፡
የምሥጠራ ሂደቱ ፐብሊክ ኪይ እና ፕራይቬት ኪይ በሚባሉ በሁለት ቁልፎች ይከናወናል፡፡ ፐብሊክ ኪይ የሚላከውን መረጃ ወደ ማይታወቅ ምሥጢራዊ ቅርጽ የምንቀይርበት ነው፡፡ ፕራይቬት የሚባለው ቁልፍ ደግሞ የተመሠጠረውን ወደ ሚነበብ ይዘት የምንመልስበት ነው፡፡ በላኪ እና ተቀባይ መካከል ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ላኪው መረጃውን በተቀባዩ ፐብሊክ ኪይ አመሥጥሮ ይልካል፡፡ የተላከው መረጃ ሊከፈት የሚችለው በተቀባዩ ፕራይቬት ኪይ ነው፡፡ ፕራይቬት ኪይ ከባለቤቱ ውጭ ለሌላ ሰው የሚጋራ ባለመኾኑ መረጃው በሌላ ሰው እንዳይከፈት ያደርጋል፡፡
በእነዚህ ሁለት ቁልፎች በሚደረግ የምሥጠራ ሂደት የመረጃው ተቀባይ ያልኾነ ሰው ራሱን እንደተቀባይ በማስመሰል የራሱን ፐብሊክ ኪይ ለላኪው ቢልክ የመረጃው ደኅንነት ችግር ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ላኪው መረጃውን መሥጥሮ የሚልከው እያስመሰለ ባለው ሰው ፐብሊክ ኪይ ስለኾነ በፕራይቬት ኪይው መክፈት ይችላል፡፡ ስለዚህ ያልተፈለገ አካል መረጃውን የማግኘት ዕድል ተፈጠረለት ማለት ነው፡፡
ይህ ችግር ይቀረፍ ዘንድ ፒ.ኬ.አይ ውስጥ ዲጂታል ሰርቲፊኬት የሚባል ማረጋገጫ አለ፡፡ ዲጂታል ሰርቲፊኬት በመረጃ ልውውጥ ጊዜ የሰዎችን ማንነት የተመለከተ ማረጋገጫ ከሚሰጥ የዲጂታል ሰርቲፊኬት ባለሥልጣን የሚሰጥ ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ በላኪ እና ተቀባይ መካከል ሌላ ሦስተኛ ወገን ሳይኖር ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡
ፒ.ኬ.አይን እውን ለማድረግ የዳታ ማዕከል ከገነቡ አፍሪካዊ ሀገራት ውስጥ ኬንያ፣ ታንዛንያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚ ሲኾኑ ኢትዮጵያም ማዕከሉን ገንብታ ሥራ ጀምራለች፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን