
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መዋጋት እና የገጠር ልማት ጉባኤ ጎን ለጎን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ተግባራት ጎብኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ግብርና በጥናትና ምርምር ተደግፎ ከተተገበረ ሀገርን በአጭር ጊዜ የመለወጥ አቅም አለው ብለዋል።
የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል ባልተገደበ የምርት እድገትና ዘላቂ የግብርና ልማቷ ዛሬ ላይ ምርታቸውን ወደ ዓለም ከሚልኩት ሀገራት ቀደሚዎች ተርታ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ከሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መዋጋት እና የገጠር ልማት ጉባኤ ጎን ለጎን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ተግባራት የመስክ ምልከታ አድርገናል ነው ያሉት።
ከዋና ከተማዋ ብራዚሊያ 1547 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ወደምትገኘው ዝናብ አጠሯ ፔትሮሊና በመጓዝ ከ40 ዓመታት በላይ በዘለቀው የሀገሪቱ የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን (Embrapa) ቅርንጫፍ የጥናትና ምርምር ጣቢያ ስር የሚሠሩ የተለያዩ ተግባራትን ተመልክተናል ብለዋል። በጉብኝታቸውም የውኃ አሰባሰብ፣ አጠቃቀም እና አሥተዳደር ሥራዎችን፤ በረሃማነትን መቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ የዘር ንፅሕና ያላቸው የእንስሳት መንጋዎችን፣ በመስኖ የሚለሙ ፍራፍሬዎች፣ የተለያዩ የዓሣ ዝርያ እርባታዎችን ማየታቸውን ነው የገለጹት።
እነዚህን ተግባራት ለመከወን የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ደጋፊ ቴክኖሎጂዎችን ጎብኝተናል ብለዋል። ኢትዮጵያ የግብርና እምቅ አቅሟን በፖሊሲ በተደገፈ፤ በልዩ አሠራርና ክትትል ቅድሚያ ሰጥታ እየወራች በአጭር ጊዜ የላቀ ውጤት እያሳየች እንደምትገኝም አመላክተዋል።
እንደ ብራዚል ያሉ የኢኮኖሚ መሠረታቸው ግብርና የሆነና ቀድመው ውጤታማ ተሞኮሮ ያላቸው ሀገራት ጋር ከፍ ባለ ትብብር አብሮ መሥራት የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው ብለዋል። ያየናቸውን ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ቀምረን ሥራ ላይ የምናውል ይሆናል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን