
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አይዲ ፎር አፍሪካ (ID4 Africa2025) ከፍተዋል። ኢትዮጵያ አይ ዲ ፎር አፍሪካ ( ID4Africa) ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና ሰብአዊ ጥረቶችን የሚያበረታቱ ጠንካራ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው የማንነት ዐውዶችን በመገንባት፣ የአፍሪካ ሀገራትን ለመደገፍ ቁርጠኛ የሆነ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ነው ተብሏል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከተበታተነው የመታወቂያ ሥርዓት አልፋ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ወደተጀመረው አስተማማኝ፣ ሁሉንም ያካተተ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መሸጋገሯን አንስተዋል።
ለፋይዳ እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። 90 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ ፋይዳ ሁሉም ዜጎች በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
እንደ ፋይናንስ፣ ጤና እና ትምህርት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች የተቀናጀው ፋይዳ፣ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ አይዲ ፎር አፍሪካን (ID4 Africa2025) በማስተናገዷ ኩራት ይሠማታል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!