የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በባሕር ዳር በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የዕለት ጉርስ ድጋፍ አደረገ፡፡

310

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ለሚገኙ 300 ሴት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የዕለት ጉርስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና እናቶች ደግሞ ድጋፉን ያገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ዱቄትና ቴምር በድጋፉ ተበርክተዋል፤ ግምታዊ ዋጋቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የማዕድ ማጋራት ድጋፉ ከዱባይ ኤምባሲ እንደተበረከተ የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ስመኝ ውቤ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ ወረርሽኙ እንደ ሀገር ያለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም በሴቶች ኅልውና ላይ የተለየ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ ሴቶች ለቤት ውስጥ ጥቃትና ያለዕድሜ ጋብቻ እየተጋለጡ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተጠናው ጥናት 40 በመቶ የአማራ ክልል ሴቶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ተገድደው እንዲያገቡ ይደረግ እንደነበርም ጠቅሰዋል፤ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዳይስፋፋ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻ ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ስለሚያደርግ ወላጆችና የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ሴቶች ለተደረገላቸው ወገናዊ አለኝታ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አማረ ዓለሙ ከተማ አስተዳደሩ ሴቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቅድመ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምግብ እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleሕዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት ያሳየውን የመተባበርና የመደጋገፍ መንፈስ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደሩ አሳሰቡ።